ዲፒ ወርልድ በበርበራ ወደብ የሚገለገሉ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች የሚጠቀሙበትን አዲስ የበይነ መረብ የግብይት ስርዓት ይፋ አደረገ
ኩባንያው በኢትዮጵያ የበይነ መረብ ግብይት ማሳለጫ የኢኮኖሚ ዞኖችን እንደሚገነባም ነው ያስታወቀው
DUBUY.com የተሰኘው ይህ ግብይት ስርዓት በገበያ እጦት የሚቸገሩ ስራ ፈጣሪዎችን ያግዛል ተብሏል
ዋና መቀመጫውን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ያደረገው ዓለም አቀፉ የሎጂስቲክስ ተቋም ዲፒ ወርልድ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካዊያን ብቻ የሚጠቀሙበት የበይነ መረብ የግብይት ስርዓት መገንባቱን አስታወቀ፡፡
የበይነ መረብ የግብይት ስርዓቱ DUBUY.com የሚሰኝ ነው ተብሏል፡፡
የግብይት ስርዓቱ የአፍሪካን ንግድ ለማቀላጠፍ በማሰብ የተቋቋመ ነው ያሉት የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሙያ ማህሙድ አል ባስታኪ ስርዓቱ እስከ 75 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ግብይትን ለመፈጸም እንዲያስችል ሆኖ መገንባቱን ለአል ዐይን ተናግረዋል።
አፍሪካ -ከአፍሪካ አገራት፤ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከአውሮፓ አገራት ጋር ጥብቅ የንግድ ትስስር እንዲኖራት በመስራት ላይ እንገኛለንም ነው ባለሙያው ያሉት።
በኢትዮጵያም ተጨማሪ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር ትናንት በአዲስ አበባ ስምምነት ፈጽሟል።
ይህ መሰረተ ልማት ሻጭ እና ገዢዎችን በቀላሉ በማገናኘት የኢትዮጵያን የወጪ እና ገቢ ንግድ እንደሚያቀላጥፈው ነው የተነገረው።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ኢትዮጵያዊያን በበርበራ ወደብ በኩል ምርቶችን እና እቃዎችን በቀላሉ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ እና ወደ ሌሎች ዓለም አቀፍ ገዢዎች ለማድረስ ይህ የግብይት ስርዓት እንደሚጠቅምም ተገልጿል።
ዲፒ ወርልድ እስከ 40 ዓመት ድረስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ የግብይት ስርዓቶችን በመስራት ላይ መሆኑንም ማህሙድ አል ባስታኪ ተናግረዋል።
ይህ የግብይት ስርዓት 127 አይነት የቢዝነስ አይነቶችን ያካተተ ሲሆን በ51 የአፍሪካ አገራት መሰረተ ልማቶች ተዘርግተዋል።
ድርጅቱ አሰራሩን ህጋዊ ለማድረግም ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆኑንም ገልጿል።
ዲፒ ወርልድ በሩዋንዳ ኪጋሊ የሎጅስቲክስ ማዕከሉን የከፈተ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በ11 አገራት የኢኮኖሚ ዞን በመገንብት ላይ መሆኑን አስታውቋል።