በዚህ ወር አዲስ አበባ በብዛት እየታዩ ያሉ የአማርኛ ፊልሞች የትኞቹ ናቸው
ሲኒማ ቤቶች በቀን ሶስት ጊዜ 8 ሰዓት፣ 10 ሰዓትና ምሽት 12 ሰዓት ላይ ለተመልካቾች እያሳዩ ይገኛሉ
የሱፍ አበባና የሰኔ ግርግር ፊልሞች እንዲሁም " ፍሬሽ ማን" ትያትር ጥሩ ተመልካች እያገኙ ነው
አራት ሚሊዮን ገደማ የህዝብ ብዛት እንዳላት የምትጠቀሰው አዲስ አበባ ነዋሪዎቿ የሚዝናኑባት ሲኒማ ቤቶችም አሏት።
የህዝብ ብዛቱን የሚመጥን መዝናናኛ ስፍራዎች ባይኖሩም ጥቂት ሲኒማ ቤቶች በያዝነው ክረምት ፊልሞች በመታየት ላይ ናቸው።
አል ዓይን በአዲስ አበባ ባሉ ሲኒማ ቤቶች ተዘዋውሮ ለእይታ የቀረቡ ፊልሞችን ዳሰሳ አድርጓል።
በደረግነው ምልከታም ከዝናብ ጋር እየታገሉ ፊልሞችን ለመመልከት ተመልካቾች ተሰልፈው አይተናል።
የመጀመሪያው ምልከታችን በቦሌ የሚገኘው ዓለም ሲኒማ ነበር። በዚህ ሲኒማ ቤት ነሀሴ ወር ከገባ ጊዜ አንስቶ "የሱፍ አበባ"፣ "ሎሌ"፣ "የሰኔ ግርግር" እና "አንድ ታሪክ" የተሰኙ ፊልሞች በሁለት ሲኒማ ክፍሎች ከእሁድ እስከ እሁድ ሁሉንም ቀናት መታየት ላይ ናቸው።
እስካሁን ባለው የተመልካቾች ብዛት "የሰኔ ግርግር እና የሱፍ አበባ የተሻለ ተመልካች ያገኙ ሲሆን ዘወትር ረቡዕ እና አርብ ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሚታየው " ፍሬሽ ማን" ትያትር ጥሩ ተመልካች እያገኘ ሲሆን በቦታ ጥበት ምክንያት ተመልካቾች አየተመለሱ መሆኑን የሲኒማ ቤቱ የደንበኞች አገልግሎት ሀላፊው አቶ ዮናስ ሀብታሙ ነግረውናል።
ሌላኛው ምልከታ ያደረግንባቸው በአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳድር ስር ያሉት ሶስት ሲኒማ ቤቶች ማለትም ሲኒማ አምፔር፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ እና አምባሳደር ሲኒማ ናቸው።
በነዚህ ሲኒማ ቤቶች "ርዕስ ፈላጊ" "የሱፍ አበባ" ፣ "አንድ ታሪክ" ፣ "ስሞት እንዳትረሺኝ" "የሰኔ ግርግር " እና "ሲመት" የተሰኙ ፊልሞች ከነሀሴ አንድ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ለተመልካቾች እየታዩ ነው።
እነዚህ ሲኒማ ቤቶች በየዕለቱ እያንዳንዳቸው ሶስት ፊልሞችን ማለትም ስምንት ሰዓት፣ አስር ሰአት እና ምሽት 12 ሰዓት ላይ ለተመልካቾች እያሳዩ ይገኛሉ።
እስካሁን ባለው የተመልካቾች ብዛት "የሰኔ ግርግር" እና "ርዕስ ፈላጊ" ፊልሞች በአንጻራዊነት የተሻለ ተመልካች ያላቸው ፊልሞች ናቸው።
ሲኒማ ቤቶቹ በሳምንት በአማካኝ አንድ አዲስ ፊልም ከፊልም ፕሮዲውሰሮች ማህበር በመቀበል ከተመልካች የሚገኘውን ገቢ እኩል እኩል እንደሚካፈሉም ሰምተናል።
ሲኒማ ቤቶች አንድን ፊልም እስከ ሶስት ወራት ድረስ ለተመልካቾች የሚያሳዩ ሲሆን ከተመልካቾች የሚሰበሰቡ አስተያየቶች እና የተመልካቾች ብዛት የፊልሞቹን የቆይታ ጊዜ እንደሚወስኑ በአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳድር ድርጅት የፊልም ፕሮግራም ባለሙያው አቶ አባይነህ ስዩም ገልጸዋል።