ፓትሪስ ሞሴፔ ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር በብሔራዊ ቤተ መንግሥት እንደሚገናኙ ይጠበቃል
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ አዲስ አበባ ገብተዋል። የካፍ መሪ ኢትዮጵያ የገቡት ዛሬ ረፋድ ላይ ነው።
ፓትሪስ ሞሴፔ ከአቶ ኢሳያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በፌዴሬሽኑ ባለቤትነት ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኘውን የካፍ የልህቀት ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡
የማዕከሉን የተለያዩ ክፍሎች እና የልምምድ ሜዳ እንዲሁም የፌዴሬሽኑን መለስተኛ ትጥቅ ማምረቻን የተመለከቱ ሲሆን በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውን እንደገለጹ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት በፌዴሬሽኑ ከሚደረግላቸው የምሳ ግብዣ በኋላ ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የሚገናኙ ይሆናል።
ከዚህ ባለፈም ፓትሪስ ሞሴፔ ከባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ጋር እንደሚወያዩም ነው ተቋማቸው ያሳወቀው።
የካፍ ፕሬዝዳንት በአዲስአበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ፕሬዝዳንቶች ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ለአንድ ቀን የሚቆዩት ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር በእግር ኳስ ከተሰማሩ የቢዝነስ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል፡፡
ሞሴፔ በቅርቡ የቡናውን አጥቂ አቡበከር ናስርን ያስፈረው የደቡብ አፍሪካው ኃያል ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ባለቤት ናቸው፡፡
ካፍ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መስፈርቶችን እንዳላሟላ በመጠቆም ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጭ እንድትጫወት መወሰኑ ይታወሳል፡፡