በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ተደረገ
ጭማሪው አንበሳ እና ሸገርን ጨምሮ ሌሎች የብዙሀን ትራንስፖርት አማራጮችን አይመለከትም ተብሏል
ዝቅተኛው ጭማሪ ሀምሳ ሳንቲም ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ እስከ ሶስት ብር ከሀምሳ ይደርሳል
በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ተደረገ፡፡
የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ይርጋለም ብርሀኔ በሰጡት መግለጫ በሚኒባስ እና ሚዲ ባስ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ተደርጓል።
በዚህም መሰረት ከዚህ በፊት በሚኒ ባስ በኪሎሜትር 2 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረው የታክሲ አገልግሎት ክፍያ ወደ ሶስት ብር ሲያድግ 30 ብር ይከፈልባቸው የነበሩት ደግሞ ወደ 33 ብር ጭማሪ ተደርጎበታል።
እንዲሁም የሚዲባስ ማለትም እስከ 37 ሰዎች ድረስ የሚጭኑ አገልግሎት ሰጪዎች 1 ብር እስከ ሁለት ብር ድረስ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል ተብሏል።
በአጠቃላይ በአዲሱ የታሪፍ ጭማሪ መሰረት ዝቅተኛው ጭማሪ ሀምሳ ሳንቲም ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ እስከ ሶስት ብር ከሀምሳ ሳንቲም ብቻ መሆኑን አቶ ይርጋለም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የታሪፍ ጭማሪው አንበሳ እና ሸገርን ጨምሮ ሌሎች የብዙሀን ትራንስፖርት አማራጮችን አይመለከትም ተብሏል።
እንዲሁም በከተማዋ ያሉ ሁሉንም የሜትር ታክሲዎችን ጨምሮ ሌሎች የቱሪስት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎች የግድ በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ መጥተው መመዝገብ እንዳለባቸው ቢሮው አሳስቧል።
ቢሮው የታሪፍ ማሻሻያው ከሰኔ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ያለ ሲሆን ህብረተሰቡ ትክክለኛውን ታሪፍ አውቆ እንዲገለገልና ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎችን እንዲያጋልጥ ጠይቋል፡፡