ሁለት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በዓለም ምርጥ የዓመቱ አትሌቶች እጩ ሆነው ቀረቡ
አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ እና አትሌት ትግስት አሰፋ በዓለማችን ምርጥ የሴት አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን 11 ምርጥ የዓመቱ አትሌቶችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል
ሁለት የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በዓለም ምርጥ የዓመቱ አትሌቶች እጩ ሆነው ቀረቡ፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተያዘው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ላይ ስኬታማ የሆኑ አትሌቶችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
11 ምርጥ የዓለማችን አትሌቶች ዝረዝር ውስጥም ኢትዮጵያዊያን ሁለት አትሌቶች የተካተቱ ሲሆን የ 5 ሺህ ሜትር ባለ ሪከርዷ ጉዳፍ ጸጋዬ እና የማራቶን ባለሪከርዷ አትሌት ትግስት አሰፋ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ አትሌቶች ናቸው፡፡
ኬንያዊቷ የ1 ሺህ 500 እና 5 ሺህ ሜትር ተወዳዳሪዋ ፌዝ ኪፕዮገን እንደ ኢትዮጵያዊያኑ በምርጥ የዓመቱ 11 አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችላለች፡፡
በቡዳፔስት የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከተሳተፉ 195 ሀገራት ሜዳሊያ ያገኙት 46ቱ ብቻ ናቸው
ከአፍሪካ አህጉር በብቸኝነት የተካተቱት ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን ብቻ ሲሆኑ የጃማያካዋ የአጭር ርቀት ተወዳዳሪ ሸሪካ ጃክሰን፣ የኔዘርላንዷ የ400 ሜትር ተወዳዳሪ ፌምኬ ቦል በእጩነት ቀርበዋል፡፡
እንዲሁም የጃፓኗ የጦር ውርወራ አሸናፊ ሃሩካ ኪታጉቺ፣ የዩክሬኗ የዝላይ ስፖርት አሸናፊ ያሮስላቫ ማሁችክ፣ የስፔኗ የ20 እና 35 ኪሎ ሜትር አሸናፊ ማሪያ ፔሬዝ፣ አሜሪካዊቷ የ100 ሜትር አሸናፊ ሻኪሪ ሪቻርድሰን፣ ቬንዙዌላዊቷ የርቀት ዘላይ ዩሊማር ሮጃስ እንዲሁም ባህሬናዊቷ የ3 ሺህ ሜትር ተወዳዳሪ ዊንፌድ ያቪ በእጩነት ከቀረቡ የዓለም ምርጥ 11 ሴት አትሌቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የውድድሩ አሸናፊ በሶት ዙር በሚካሄድ ማጣሪያ የምትታወቅ ሲሆን ተሳታፊዎች በኢሜይል እና በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰጥ ድጋፍ ይወሰናል ተብሏል፡፡
እንዲሁም የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት ለእጩ ተወዳዳሪዎች የ50 በመቶ ነጥብ ይሰጣል የተባለ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰጥ ነጥብ ደግሞ ከ25 በመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡
የመምረጫ ጊዜ እስከ ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓም ይቆያል የተባለ ሲሆን የመጨረሻ አሸናፊ ምርጥ የዓመቱ ሴት እና ወንድ አትሌቶች ምርጫ ደግሞ ከህዳር 2-3 ቀን 2016 ዓም ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡