አትሌት ጥላሁን ሀይሌ ያላግባብ ከውድድር አለመቀነሱን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ
አትሌት ጥላሁን ከዓለም አትሌቲክስ የ5 ሺህ ሜትር ውድድር የተቀነሰበት መንገድ ቅሬታ እንደፈጠረበት ተናግሯል
በሀንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እስካሁን 6 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከአለም 4ኛ ደረጃን ይዛለች
አትሌት ጥላኩን ሀይሌ ያላግባብ ከውድድር አለመቀነሱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ።
በሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ አንዷ ተሳታፊ ሀገር ነች።
በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በ5 ሺህ ሜትር ውድድር ተመርጠው ወደ ስፍራው ከተጓዙ አትሌቶች መካከል ጥላሁን ሀይሌ ይገኝበታል።
ይህ አትሌት ከውድድሩ ማጣሪያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ " በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ ውሳኔ ከውድድሩ ተቀንሻለሁ" ሲል ቅሬታ አሰምቷል።
አትሌቱ አክሎም "ሀገሬን ለማስጠራት ሌት ተቀን ልምምድ ሳደርግ ቆይቼ እና መስፈርቱን አሟልቼ ብመረጥም ውድድሩ ሲቀርብ ከውድድሩ መቀነሴ ተነገረኝ፣ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፈጸመብኝን ግፍ እና በደል የኢትዮጵያ ህዝብ ይወቅልኝ" ሲልም አስታውቋል
ይህን ቅሬታ መሰረት በማድረግ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ በቡዳፔስት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቷ "ጥላሁን ስላዘንክ ፤ ስለተበሳጨህ በጣም ይቅርታ" ያለች ሲሆን "ይቅርታ የምለው በጣም ስላለቀሰ ስላዘነ ነው ፤ ነገር ግን መብቱን አልነካንም ፤ እሱን አስወጥተን ማንንም አላስገባም። ሁሉም ባላቸው ሰዓት እና በብቃታቸው ነው የገቡት " በሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
"የአትሌቱን መብት ነክተን አላስቀረነውም 4ኛ በመሆኑ ብቻ ነው ከውድድሩ ያስቀረነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
ውሳኔዎች የሚተላለፉት በጋራ እና በኮሚቴ እንጂ በተናጠል አለመሆኑን በመጥቀስም "ወደ ውድድር የማስገባው እና የማስወጣው አትሌት የለም" በማለት አብራርተዋል።
አትሌት ጥላሁን ኃይሌ የማይወዳደር ከሆነ ለምን ወደ ውድድር ስፍራው እንዲጓዝ ተደረገ በሚል ለቀረበው ጥያቄም "ምናልባት በሪሁ የሆነ ነገር ቢሆን የሱ መኖር አስፈላጊ ነው ፤ ተጠባባቂ አትሌት ሁሌም ይኖራል፣ ይህ ድሮም የነበረ የቆየ አሰራር ነው" በሚል ምላሽ ተሰጥቷል።
በሀንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እስካሁን 6 ሜዳሊያዎችን (1የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሃስ) በመሰብሰብ ከአለም 4ኛ ደረጃን ይዛለች።