አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ልዩ መልዕክተኛ ሾመች
ጄፍሪ ፌልትማን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ተደርገው መሾማቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት በቅርበት የሚከታተሉ ይሆናል
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ መሾሟ ተነግሯል።
አዲሱ የኃላፊነት ስፍራ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተፈጠረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል ያለውን አለመግባባት በቅርበት ለመከታተል የታለመ መሆኑም ታውቋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትናነትናው እለት ጄፍሪ ፌልትማን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ተደርገው መሾማቸውን አስታውቀዋል።
አንቶኒ ብሊንከን በመግለጫው አክለውም አሁን ላይ አሜሪካን የሚያሳስበው ነገር ቢኖር የትግራይን ግጭትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ያለው ተለዋዋጭ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው የመጣ የድንበር ውጥረት እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው ውዝግብ ነው ብለዋል።
ጄፍሪ ፌልትማን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸውም የባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ተያያዥ የሆኑትን ፖለቲካዊ፣ የደኅንነትና የሰብአዊ ጉዳዮች ምፍትሔ እንዲያገኙ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክትም አስታውቀዋል።
የ62 ዓመቱ አዲሱ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ላይ አገልግለዋል።
በፈረንጆቹ ከ2004 እስከ 2009 በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆንም የሰሩ ሲሆን፤ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በጆርዳን፣ በሀነጋሪ እና በሀይቲ በዲፕሎማትነት አግልግለዋል።