አሜሪካ ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፎች የሚውል የ52 ሚልዮን ዶላር እርዳታ አደረገች
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲበጅለት ጥሪ አቅርበዋል
ዋሽንግተን ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቃለች
ኢትዮጵያበሰሜናዊ ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ፤ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሰብአዊ እርዳታዎችን ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ አሁንም የተፈጠረውን ችግር ለማቃለል የሚያስችል የ52 ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ እንደምታደርግም ነው፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ይፋ ያደረጉት፡፡
አሜሪካ አስካሁን ለትግራይ ክልል በአጠቃላይ የ153 ሚልዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡
ድጋፉ ችግሩን ከማቃለልም በላይ ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች እጃቸውን እንዲዘረጉ የሚያነሳሳ ተግባር ነው ብሏል ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የተገኘው መግለጫ፡፡
በክልሉ አሁን ላይ 4 ነጥብ 5 ሚልዮን ገደማ ህዝብ ለከፋ ችግር መዳረጉ ይነገራል፡፡
ፈንዱ በጦርነቱ ምክንያት የተጠፋፉ ቤተሰቦች የሚገናኙበትን ማእቀፍ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ነው የሃገራቸው የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሰጪ ድርጅት (DART) ወደ ትግራይ ማቅናቱን የጠቆሙት ብሊንከን የገለጹት፡፡
በክልሉ ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ያሳስበናልም ብለዋል ፡፡
ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ላለው ጥረት እውቅና እንደሚሰጡ የገለጹም ሲሆን አለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ላይ የተቀመጠው ገደብ እንዲነሳ እንዲሁም የድርጅቶቹ ሰራተኞች የቆይታ ቪዛ እንዲራዘም ከማድረግ ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮች በትኩረት ሊከታተላቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ጉዳይ ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልተበጀለት ችግሩ በከፋ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ያስቀመጡት ሚኒስትሩ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ፣ የኤርትራ ወታደሮች እና መንግስት በክልሉ ያሰማራቸው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት መውጣት ቀድመው ሊወሰዱ የሚገባቸው ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው ብለዋል፡፡
አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግስት በተናጠልም ሆነ ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን በትግራይ ተፈፀሙ ስለተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች ለማጣራት እያደረገው ያለ ተግባር የሚበረታታና አሜሪካ በቅርበት እየተታተለችው ያለ ጉዳይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ለጋሽ ድርጅቶች በትግራይ የገጠመውን ቀውስ ለማቃለል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡