የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ አሜሪካ አሳሰበች
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸው ተገልጿል
"የአማራ ኃይሎች እና የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ እና ውጊያው በፍጥነት እንዲቆም" የውጭ ጉ/ሚኒስትሩ ጠ/ሚ ዐቢይን ጠይቀዋል
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን ዛሬ የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ በድረገጹ ይፋ እንዳደረገው፣ በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ አገልግሎት ችግር እና የሰብዓዊ መብት ቀውስ አሜሪካን እንደሚያሳስባት አፅንዖት ለመስጠት ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይን ያናገሩት፡፡
"የጭካኔ ድርጊቶች ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና በደሎች መኖራቸውን የሚያመለክቱ ተዓማኒነት ያላቸው ሪፖርቶች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን" በመግለጽ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ ፈጣን እና ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም ተጨማሪ ቀውስ እንዳይከሰት ብሊንከን ማሳሰባቸው ነው የተገለጸው።
ሚኒስትሩ ብሊንከን ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ያነሱትን ነጥብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድገም ፣ በዛሬው መግለጫ የውጭ ኃይሎች ተብለው የተጠቀሱት "የአማራ ኃይሎች እና የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ እና ውጊያው በፍጥነት እንዲቆም ግፊት አድርገዋል" ተብሏል፡፡
ሚስተር ብሊንከን የአማራ ልዩ ኃይልን በመጥቀስ መግለጫ መስጠታቸውን ፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራ እንደሆነ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን እንደሆነ እና መንግስት በሀገሪቱ ግዛት ከጫፍ እስከጫፍ የትኛውንም በሀገሪቱ ያለ የፀጥታ መዋቅር የማሰማራት ስልጣን እንዳለው መግለጹ ይታወሳል።
ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ላይ ገለልተኛ ፣ ዓለም አቀፋዊ እና ተዓማኒ ምርመራዎችን ለማመቻቸት እና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር እንዲሰራም ሚስተር ብሊንከን ጠ/ሚ ዐቢይን ጠይቀዋል በመግለጫው እንደተጠቀሰው፡፡
በቅርቡ በትግራይ ሙሉ እና ያልተገደበ የሰብአዊ መብት ተደራሽነት በኢትዮጵያ መንግስት ለመፈቀዱ የአሜሪካው ሚኒስትር እውቅና ሰጥተዋል፡፡ መግለጫው እንደሚለው ፣ መንግስት በሰብዓዊ መብት ተደራሽነት ዙሪያ የገባውን ቃል አክብሮ መቀጠሉ አስፈላጊ መሆኑን በአጽንዖት አንስተው ፣ አሜሪካ ግጭቱን ለመፍታት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል። አሜሪካ በመላው ኢትዮጵያ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሕይወት አድን ሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗንም አስረድተዋል ብሏል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፡፡
ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ጠ/ሚ ዐቢይ በየትኞቹ ነጥቦች ላይ እንደተስማሙ ፣ አሊያም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ምን እንደሆነ በመግለጫው ላይ የተባለ ነገር የለም። በኢትዮጵያ መንግስት በኩልም ወዲያው የተሰጠ ምላሽ የለም።