“የኤርትራ ኃይሎች እና የአማራ ክልል ኃይሎች በአፋጣኝ ከትግራይ ክልል መውጣት አለባቸው” የአሜሪካ ውጭ/ጉ/ሚኒስትር
አሜሪካ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገልጸዋል
ኢትዮጵያ በትግራይ ያልተገደበ የሰብአዊ አገልግሎት መፍቀዷን እና ለመብት ጥሰት ምርመራዎች ዓለም አቀፍ ድጋፍን ለመቀበል መዘጋጀቷን አሜሪካ ተቀብላለች
አሜሪካ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በትግራይ ያልተገደበ የሰብአዊ አገልግሎት መፍቀዷን እና ለመብት ጥሰት ምርመራዎች ዓለም አቀፍ ድጋፍን ለመቀበል መዘጋጀቷን አሜሪካ ተመቀበሏንም አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ተብለው ሪፖርት የተደረጉ የወንጀል ተግባራት እና የክልሉ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱ አሜሪካን እንዳሳሰባት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ባወጡት መግለጫ “በርካታ ድርጅቶች ሪፖርት ያደረጓቸውን እና በብዙ አካላት የተፈጸሙ ግድያዎችን ፣ አስገዳጅ መፈናቀል ፣ የወሲብ ጥቃቶች እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎችን አጥብቀን እናወግዛለን” ብለዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሺናል ከትናንት ወዲያ ባወጣው መግለጫ የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ከተማ በንጹኃን ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ገልጾ ይህ ግድያ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን ይችላል ብሏል።
የድርጅቱን ሪፖርት ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአምነስቲ ሪፖርት ግብአት የሆኑ መረጃዎች በምሥራቅ ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞችና አክሱም ውስጥ ካሉ ግለሰቦች በስልክ የተሰበሰቡ ውስንነት ያለባቸው ምንጮች መሆናቸውን ገልጾ ከስደተኞች መካከልም አንዳንዶቹ የሕወሓት የቀድሞ ተዋጊዎች የነበሩ ናቸው ብሏል። በመሆኑም በአምነስቲ የወጣው ሪፖርት "ባልተሟላ መረጃና ውስን በሆነ የጥናት ዘዴ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው" ሲል አጣጥሎታል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደ ማይካድራው ሁሉ ምርመራ እንደሚደረግባቸው አስታውቋል፡፡ የኤርትራ መንግስትም የአምነስቲን ሪፖርት ተዓማኒነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ እንደማያቀበለው አስታውቋል፡፡
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በትግራይ “እየተባባሰ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ በጣም ያሳስበናል” ያሉ ሲሆን“ሁከትና ብጥብጥን ማስቆም እና ያልተገደበ የሰብዓዊ መብት ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ፣ ተፈጽመዋል ተብለው በተዘገቡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የተሟላ ፣ ገለልተኛ ፣ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲደረግ አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግሥት ደጋግማ አነጋግራለች” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ፣ በሕግ እንዲጠየቁ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
“ያልተገደበ የሰብአዊ አገልግሎት ተደራሽነት ስለመፈቀዱ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ላይ ለሚደረጉ ምርመራዎች ዓለም አቀፍ ድጋፍን ለመቀበል ኢትዮጵያ ዝግጁ ስለመሆኗ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ. የካቲት 26 ያወጡትን መግለጫ አሜሪካ ትቀበላለች” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡ እነዚህ ቃል ኪዳኖች እውን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ መሥራት አለበት ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ምንም እንኳን የኤርትራም ይሁን የኢትዮጵያ መንግስታት በትግራይ ክልል የኤርትራ ሰራዊት መኖሩን ባይቀበሉም አሜሪካ አሁንም ድረስ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል እንዳሉ ነው የምታምነው፡፡ “የኤርትራ ኃይሎች እና የአማራ ክልል ኃይሎች በአፋጣኝ ከትግራይ ክልል መውጣት ቀዳሚ እርምጃዎች መሆን አለባቸው” ብለዋል ብሊንከን፡፡ “በመቀጠልም በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች ጸብ እንዲቆም በማድረግ በትግራይ ያለመስተጓጎል ዕርዳታ እንዲደርስ በቁርጠኝነት መፍቀድ አለባቸው” ብለዋል፡፡ “እነዚህን ግቦች ለማሳካት አሜሪካ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ናት” ያሉም ሲሆን ለዚህም ዩኤስኤአይዲ (USAID) የነፍስ አድን ዕርዳታ ማድረጉን ለመቀጠል የአደጋ ድጋፍ ምላሽ ቡድንን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያሰማራ ገልጸዋል፡፡
“ዓለም አቀፍ አጋሮች በተለይም የአፍሪካ ህብረት እና ቀጣናዊ አጋሮች በትግራይ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ከእኛ ጋር እንዲሰሩ እንጠይቃለን” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ዘላቂ የሆነ አጋርነት ለመገንባት ቁርጠኛ እንደሆነችም ሚኒስትሩ መግለጻቸውን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በድረገጹ አስታውቋል፡፡