የ81 አመቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የቲክቶክ አካውንት ከፈቱ
ባይደን በ2022 በመንግስት ተቋማት ጥቅም ላይ እንዳይውል ያገዱትን ቲክቶክ መጠቀም የጀመሩት በቀጣዩ ምርጫ የተሻለ ድምጽ ለማግኘት በማሰብ ነው ተብሏል
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በቅርቡ ቲክቶክን መቀላቀላቸው ይታወሳል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቲክቶክ አካውንት ከፍተው ቪዲዮ ማጋራት ጀምረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቲክቶክ በመንግስት ተቋማት ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚያግድ ህግ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ የደህንነት ስጋት ደቅኗል በሚል ያሳለፉት ውሳኔን ተከትሎ በርካታ የፌደራል ተቋማት ይህን መተግበሪያ በቢሮ ውስጥ መጠቀም መከልከላቸው አይዘነጋም።
በያዝነው የፈረንጆቹ አመት የሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ግን ባይደን ራሳቸው የቲክቶክ አካውንት ባለቤት እንዲሆኑ ያስገደደ ይመስላል።
በአሜሪካ ከ150 ሚሊየን በላይ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች በመኖራቸው በማህበራዊ ትስስር ገጹ የተለያዩ ቪዲዮዎችን በማጋራት በምርጫው የተሻለ ድምጽ ለማግኘት ማሰባቸው ነው የተነገረው።
የፕሬዝዳንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን "@bidenhq" የሚል ስያሜ ያለው የቲክቶክ አድራሻ ከፍቶ የባይደን የመጀመሪያውን የቲክቶክ ቪዲዮ ተለቋል።
የ81 አመቱ ፕሬዝዳንት በከፈቱት አዲስ የቲክቶክ አካውንት በ24 ስአት ውስጥ ከ46 ሺህ በላይ ተከታይ ያገኙ ሲሆን፥ የለቀቁት ቪዲዮም ከ4 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ተመልካች አግኝቷል።
የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የባይደን የማስታወስ ችሎታ ጥያቄ ውስጥ መውደቁንና ሚስጢራዊ መረጃዎችን አያያዛቸውም ሊመረመር ይገባል ማለቱ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው እየተነገረ ነው።
በቲክቶክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው አሜሪካ ቤጂንግ የተጠቃሚዎቹን መረጃ ልትበረብር ትችላለች በሚል ስታቀርብ የነበረውን ወቀሳና እገዳ ወደጎን በማለት ለፕሬዝዳንቷ የቲክቶክ አካውንት ከፍታለች።
የባይደን የቲክቶክ አካውንትን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው ያስተዳድረዋል የተባለ ሲሆን፥ ድርጊቱ ፖለቲከኞች ወጣቶችን ለሚያገኙባቸው የማህበራዊ ትስስር ገጾች የሰጡትን ትኩረት ያሳያል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በቅርቡ ቲክቶክን መቀላቀላቸው አይዘነጋም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮች ባገኙበት የቲክቶክ አካውንታቸው የተለያዩ ቪዲዮዎችን እያጋሩ ነው።