በቲክቶክ ፉክክር ህይወቱን ያጣው አሜሪካዊ፤ ሚስቱ ህልፈቱን ቀርጻለች
ግለሰቡ ከሚበር ጀልባ ላይ በመዝለል የሚደረግ የቲክቶክ ፉክክር (ቻሌንጅ) ሲያደርግ ነው ህይወቱ ያለፈው
መሰል የቲክቶክ አጉል ፉክክሮች ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የአራት ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል ተብሏል
በአሜሪካ አላባማ ሚስት የባሏን ህልፈት በቪዲዮ ቀርጻ ማስቀረቷ ተነግሯል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብ በቲክቶክ ተከታዮቹን ለማስደመም ከሚበር ጀልባ ላይ በመዝለል ወደ ባህር ተወርውሮ ነው ውዱን ህይወቱን ያጣው።
በቲክቶክ የተለየ ነገር በማድረግ ተከታዮችን ለማብዛት የሚደረግ ፉክክር የበርካቶችን ህይወት መቀማቱ ይነገራል።
በፍጥነት ከሚበር ጀልባ ላይ በመዝለል ወደ ባህር የመግባት ፉክክር (#boatjumping ቻሌንጅ) በየካቲት ወር በአላባማ ኮሳ ባህር ውስጥ አንድ ወጣትን ለህልፈት መዳረጉን ሚረር አስታውሷል።
ባለፉት ስድስት ወራት በአሜሪካ ብቻ አራት ሰዎች በዚህ የቲክቶክ ፉክክር (ቻሌንጅ) አንገታቸው ተሰብሮና ጭንቅላታቸው ከጥቅም ውጭ ሆኖ ህይወታቸው ማለፉም ተዘግቧል።
በአላባማ የባህር ላይ ነፍስ አድን ባለሙያዎች ሃላፊው ካፒቴን ጂም ዴኒስ፥ “በተልካሻ የቲክቶክ ፉክክር ሰዎች ህይወታቸውን ማጣት መቀጠላቸው አሳዛኝ ነው” ብለዋል።
ከፈጣን ጀልባዎች ላይ ወደ ባህር የሚዘሉ ሰዎች ከሞት ቢተርፉ እንኳን ፓራላይዝ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም በመጥቀስ።
ሰዎች ካሜራ ፊት ለጓደኞቻቸው እና ተከታዮቻቸው ያልሆኑትን ሆነው ለመታየት የሚያደርጉት አደገኛ ልማድ ሚስት የባሏን ህልፈት እንድትቀርጽ ማድረጉንም ነው ካፒቴን ጂም ያነሱት።
የአላባማ ፖሊስ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ይህን መሰሉን አደገኛ ፉክክር ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ከፈጣን ጀልባ ላይ መዝለል ከህንጻ ላይ እንደመውደቅ ከባድ አደጋ እንዳለው በመጥቀስም ማስጠንቀቂያውን ቢያወጣም የአራቱ ሰዎች ህልፈት በቲክቶክ የራሳቸውን አለም ለመፍጠር የሚሯሯጡ ወጣቶች ቁብ ይሰጡታል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
ከ1 ቢሊየን በላይ ወርሃዊ ተጠቃሚ ያለው ቲክቶክም ከጀልባ ላይ የመዝለል ፉክክሩ አደገኛነቱን ቢያስቀምጥም ከ2020 ጀምሮ በርካቶች ሲሞክሩት ያገኙት ተመልካች በጣም የበዛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።