ባይደን እና ኔታንያሁ በኢራን ላይ ስለሚፈጸመው ጥቃት መከሩ
መሪዎቹ በሊባኖስ እየተካሄደ ባለው ውጊያ ዙሪያም የተወያዩ ሲሆን፥ ባይደን የእስራኤል የአየር ጥቃት በንጹሃን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እንዲቀንስ አሳስበዋል
እስራኤል በሶሪያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሄዝቦላህ አባላትን መግደሏን አስታውቃለች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል በኢራን ላይ ልትወስደው ስላቀደችው የአጻፋ ጥቃት መከሩ።
ሁለቱ መሪዎች ለ30 ደቂቃ በስልክ ባደረጉት ምክክር የአጻፋ ጥቃቱ ተገቢነት ላይ መስማማታቸውን ዋይትሃውስ ገልጿል።
እስራኤል ከባላንጣዋ ኢራን በቅርቡ ለደረሰባት የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ምን አይነት አጻፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ አልተገለጸም።
ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው ሳምንት እስራኤል የኢራን የነዳጅ እና የኒዩክሌር ጣቢያዎች እንዳታጠቃ ጥሪ ማቅረባቸው ቢነገርም ቴል አቪቭ የቴህራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ኢላማ ልታደርግ እንደምትችል ይጠበቃል።
ተንታኞች እስራኤል የኢራንን የባለስቲክ ሚሳኤል ማምረቻ ጣቢያዎች እና የአየር መቃወሚያ ስርአቶች ልትመታ እንደምችል መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት “ የእኛ (እስራኤል) ጥቃት እልቂት የሚያስከትል፣ ኢላማውን የሚመታና ከሁሉም በላይ የማይጠበቅ ይሆናል” ማለታቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ኢራን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ከእስራኤል የሚቃጣ የአጻፋ እርምጃ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል ስትል መዛቷ የሚታወስ ነው።
እስራኤል በሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር የምታደርገው የምድር ውጊያ እና በቤሩትና ሌሎች ከተሞች የምትፈጽመው የአየር ጥቃትም ባይደን እና ኔታንያሁ ከመከሩባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በዚሁ ወቅት እስራኤል በሊባኖስ የምፈጽመው የአየር ጥቃት በንጹሃን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እንዲቀንስ አሳስበዋል ብሏል ዋይትሃውስ ባወጣው መግለጫ።
በተያያዘ ዜና እስራኤል በቤሩት የምትፈጸመው የአየር ጥቃትና በደቡባዊ ሊባኖስ የሚካሄደው ውጊያ ቀጥሎ ወደ ሶሪያም ተሻግሯል።
የእስራኤል የጦር ጄቶች በሶሪያ በኢራን ድጋፍ ይደረግላቸዋል በተባሉ ቡድኖች እና የሄዝቦላህ አባላት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የሀገሪቱ ጦር ገልጿል።
በሶሪያ ቁኔትራ በተባለ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት የሄዝቦላህ ክንፍ የሆነው “ጎላን ቴረሪስት ኔትወርክ” አባል የሆነውና ለሄዝቦላህ መረጃ የሚያቀብለው አድሃም ጃሁት ተገድሏል ብሏል ጦሩ ባወጣው መግለጫ።
የሶሪያ ብሄራዊ ቴሌቪዥን በበኩሉ እስራኤል በሆምስ እና ሃማ ከተሞች አቅራቢያ የተፈጸሙት የአየር ጥቃቶች “መጠነኛ የንብረት ውድመት” ማስከተላቸውን ዘግቧል።
እስራኤል በኢራን ይደገፋሉ የምትላቸው የፍልስጤም፣ የሊባኖስ፣ የሶሪያ፣ የየመን እና የኢራቅ ታጣቂ ሃይሎች የተቀናጀ ጦርነት ከፍተውብኛል ብላ ታምናለች። በጋዛ ከሃማስ ጋር ጦርነት ከጀመረች አንስቶም በሶሪያ እና የመን ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን ማድረሷ ይታወሳል።