እስራኤል ለምትፈጽመው ጥቃት የባህረ ሰላጤው ሀገራት የአየር ክልላቸውን እንዳይፈቅዱ ኢራን አስጠነቀቀች
በገልፍ ሀገራት ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የአየር ክልላቸውን በሚፈቅዱት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል
ኢራን የአሜሪካ የጦር ካምፖች የሚገኙባቸው የቀጠናው ሀገራት እንቅስቃሴን በአንክሮ እንደምትከታተል ገልጻለች
እስራኤል ትፈጽመዋለች ተብሎ ለሚጠበቀው የአጸፋ ምላሽ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት የአየር ክልላቸውን እንዳይፈቅዱ ኢራን ማስጠንቀቋ ተሰምቷል፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ሚንስትር አባስ አራግቺ ሳኡዲ አረቢያ እና ኳታርን ጨምሮ በሌሎች የባህረሰላጤው ሀገራት ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ሚንስትሩ ቢዚህ ወቅት ለእስራኤል ጥቃት የአየር ክልልን ክፍት ማድረግ እርምጃ ሊያስወስድ የሚችል ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
የትኛውንም የገልፍ ሀገር የአየር ክልልም ሆነ ወታደራዊ ካምፕ መነሻ አድርጎ በኢራን ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ቴሄራን ከሁሉም የገልፍ ሀገራት የተቃጣ ጥቃት አድርጋ እንደምትወስደው አስጠንቅቃለች፡፡
ከዚህ ባለፈም በቀጠናው ሁሉን አቀፍ ጦርነት ለማስነሳት ጥረት እያደረገች ነው ባሏት እስራኤል በተቃራኒ ቀጠናው በህብረት መቆም እንደሚገባው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አስምረው ተናግረዋል፡፡
ኢራን እስካሁን ባለው በገልፍ ሀገራት የነዳጅ ማውጫዎች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም በግልጽ ባትናገርም የአካባቢው የእስራኤል ወዳጆች ለጥቃቱ ተባባሪ የሚሆኑ ከሆነ የትኛውም ኢላማ ላይ ጥቃት ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማትል መናገሯን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ የአሜሪካ የጦር ካምፖች የሚገኙባቸው ባህሬን ፣ ኩዌት ፣ ኳታር ፣ ሳኡዲ አረብያ እና አረብ ኤሜሬትስ በኢራን ላይ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት የነበራቸውን እንቅስቃሴ እና የሚሰጡትን ምላሽ በቅርበት እንከታተላለን ነው ያሉት፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዛሬው እለት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር የስልክ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቴልአቪቭ የተሄራንን የነዳጅ ማውጫ እና የኒውክሌር ማብላያ ጣብያዎችን ልታጠቃ እንደምትችል ከፍተኛ ስጋት ያላት ዋሽንግተን የአጸፋ ምላሹ ሊያሰከትለው የሚችለውን ውጥረት እና ተጽእኖ ለመቀነስ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡
የዛሬው ከባይደን ወደ ኔታንያሁ የሚደረገው የስልክ ጥሪም በዚሁ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ እስራኤል በምትሰጠው የአጸፋ ምላሽ ኢላማ ያደረገችባቸውን ስፍራዎች ለውጥ እንድታደርግ እየጠየቀች ትገኛለች፡፡
የነዳጅ ላኪ አባል ሀገራት ህብረት (ኦፔክ) ሰብሳቢ የሆነችው ሳኡዲ አረቢያ ግጭቱ ተባብሶ በኢራን ላይ ጥቃትን የሚያስከትል ከሆነ በአለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም በቂ የነዳጅ ክምችት መኖሩን ተናግራለች፡፡