“ኢራን የኒዩክሌር ቦምብ ለመስራት አንድ ሳምንት ብቻ ይበቃታል” - የአሜሪካ የስለላ ድርጅት
የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ አሜሪካ የቴህራንን የዩራኒየም ማበልጸግ ሂደት በጥብቅ እየተከታተለች ነው ብለዋል
እስራኤል ለባለፈው ሳምንቱ የኢራን የሚሳኤል ጥቃት ምላሽ እንደምትሰጥ ማስጠንቀቋ ይታወሳል
ኢራን አቶሚክ ቦምብ ለመስራት መቃረቧን የአሜሪካው የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ገለጸ።
የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ ቴህራን የኒዩክሌር ቦምብ ለመስራት “አንድ ሳምንት ብቻ ይበቃታል” ማለታቸውን የአሜሪካው ኤንቢሲ ዘግቧል።
እስራኤል ለባለፈው ሳምንት የኢራን የሚሳኤል ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ በሚጠበቅበት ወቅት ነው የአሜሪካ የስለላ ድርጅት የቴህራን የኒዩክሌር አቅም መጎልበቱን የሚጠቁም መረጃ ያወጣው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቴህራን ላይ እንወስደዋለን ባሉት የአጻፋ ምላሽ ውስጥ ስለመካከቱ ባያነሱትም ቴል አቪቭ የኢራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ልትመታ እንደምትችል ሲዘገብ ቆይቷል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም እስራኤል ለምትፈጽመው ጥቃት የከፋ አጻፋዊ ምላሽ ይኖራል ሲል አስጠንቅቋል።
በጆርጂያ ሲ አይስላንድ እየተካሄደ በሚገኘው የደህንነት ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ ኢራን የኒዩክሌር የጦር መሳሪያዎች ባለቤት ለመሆን ስላሳለፈችው ውሳኔ አዲስ መረጃ የለም ቢሉም፥ የዩራኒየም ማበልጸግ ሂደቷ የኒዩክሌር የጦር መሳሪያዎችን ለመስራት በሚያስችል ደረጃ መፋጠኑን ተናግረዋል።
ኢራን የኒዩክሌር መሳሪያ ለማልማት ከወሰነች ግን አሜሪካ እና አጋሮቿ እንቅስቃሴዋን በፍጥነት እንደሚደርሱበት ነው የገለጹት።
የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ሀገራቸው አውዳሚውን የኒዩክሌር መሳሪያ መታጠቅ እንደማትፈልግ ደጋግመው ቢገልጹም ወቅታዊው ውጥረት የቀደመ አቋማቸውን ሊያስቀይራቸው እንደሚችል ይገመታል።
“ኢራን አቶሚክ ቦምብ ለመስራት ከወሰነች በአጭር ጊዜ እውን ታደርገዋለች፤ የውጪው አለም ግን ምላሽ ለመስጠት ጊዜ አይኖረውም” ያሉት በርንስ፥ አሜሪካ የኢራንን የኒዩክሌር መሳሪያ ልማት እንቅስቃሴ በአንክሮ እንደምትከታተል ተናግረዋል።
አሜሪካ በአወዛጋቢው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን (በ2018) ከ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት መውጣቷና ቴህራን የተነሱላትን ማዕቀቦች በድጋሚ መጣላቸው ይታወሳል።
ይህ ስምምነት ተፈጻሚ በነበረበት ወቅት ኢራን አንድ አቶሚክ ቦምብ ለመስራት የሚያስፈልጋትን በደንብ የተብላላ ዩራኒየም ለማከማቸው ከአንድ አመት በላይ ያስፈልጋት ነበር የሚሉት የሲአይኤ ዳይሬክተር፥ አሁን ግን አንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ቀናት ብቻ በቂዋ ነው በማለት ስጋቱ ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢራን ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ ወይንም አቶሚክ ቦምብ ለመስራት ምን ያህል ጊዜ ይወስድባታል የሚለው በተለያዩ አካላት የተለያየ ግምት ይሰጠዋል።
አብዛኞቹ የምዕራባውያን የደህንነት ባለሙያዎች ግን ቴህራን የኒዩክሌር አረር ለመስራት አንድ አመት ሊወስድባት እንደሚችል ነው የሚስማሙት።