ኔታንያሁ ሊባኖስ እንደ ጋዛ ልትፈራርስ እንደምትችል አስጠነቀቁ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊባኖሳውያን ሀገራቸውን ከመፈራረስ ለመታደግ ሄዝቦላህን ማስወገድ እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት
ሄዝቦላህ ለሶስተኛ ተከታታይ ቀን ወደ እስራኤሏ የወደብ ከተማ ሃይፋ ሮኬቶችን ተኩሷል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሊባኖሳውያን ሀገራቸውን እንደ ጋዛ ከመፈራረስ እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኔታንያሁ ለሊባኖስ ህዝብ በቪዲዮ የተቀረጸ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እስራኤል ወደ ደቡብ ምዕራባዊ ሊባኖስ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በመላክ አዲስ የጦርነት ግንባር ከፍተው ነው ለሊባኖስ ዜጎች መልዕክት ያስተላለፉት።
የእስራኤል ጦር ሰኞ እለት በፈጸመው የአየር ጥቃት 50 የሄዝቦላህ አባላት መገደላቸውን አስታውቋል።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ባለፉት 24 ስአታት በእስራኤል ጥቃት 36 ሊባኖሳውያን መገደላቸውንና ከ150 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።
ሄዝቦላህም ወደ እስራኤሏ የወደብ ከተማ ሃይፋ ለሶስተኛ ተከታታይ ቀን ሮኬቶችን መተኮሱና 12 ሰዎች መቁሰላቸው ነው የተነገረው።
ኔታንያሁ በትናንቱ የቪዲዮ መልዕክታቸው “(ሊባኖሳውያን) ሀገራችሁን ከረጅምና እንደ ጋዛ ሊያፈራርሳት ከሚችል ጦርነት የመታደግ እድል አላችሁ፤ ሀገራችሁን ከሄዝቦላህ ነጻ አውጡና ጦርነቱ ይጠናቀቅ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የናስራላህ ተተኪ ሆነዋል የተባሉትን ሃሽም ሰይፈዲን መገደላቸውን ቢያነሱም የእስራኤል ጦር ግን ግድያውን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ከንግግራቸው በኋላ መግለጫ አውጥቷል።
ለሶስት ሳምንታት በእስራኤል ከባድ ጥቃት የደረሰበት ሄዝቦላህ የጋዛው ጦርነት እስካልቆመ ድረስ ወደ እስራኤል ሮኬትና ሚሳኤሎችን መተኮሱን እንደማያቋርጥ አስታውቋል።
የናስራላህ የቀድሞው ምክትል ናይም ቃሴም በትናንትናው እለት በሰጡት ማብራሪያ በእስራኤል ድብደባ የሄዝቦላህ አቅም እንዳልተጎዳና በምድር ውጊያውም በርካታ የእስራኤል ወታደሮችን መግደሉን መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ከ15 ሺህ በላይ ወታደሮቿን ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ያስገባችው እስራኤል በበኩሏ በድንበር ከተማዋ ማሩን አል ራስ የሄዝቦላህን ማዘዣ ጣቢያ መቆጣጠሯን ገልጻለች።
የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሊባኖሳውያንን ከመኖሪያቸው ያፈናቀለው የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት እንዲቆም ጥሪ እያስተላለፉ ነው።
በጦርነቱ በሺህ የሚቆጠር ሄክታር የእርሻ መሬት መቃጠሉን የጠቀሰው የአለም ምግብ ፕሮግራምም ሊባኖስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የለጋሾችን እጅ መመልከቷ እንደማይቀር ነው የገለጸው።
የእስራኤል የአየር ድብደባና የምድር ውጊያ መጠናከር ሄዝቦላህን ለተኩስ አቁም እንደሚያስገድደው ቢጠበቅም እስራኤል ግን እንደ ሃማስ ሁሉ ሄዝቦላህም ካልጠፋ ሰላም አላገኝም በማለት ውጊያው እንዲቀጥል ማድረጓና ሊባኖስም እንደ ጋዛ መፈራረሷ አይቀርም የሚለው የበርካቶች ስጋት ነው።