ባይደን ለድሀ ሀገራት የሚከፋፋል 4 ቢሊየን ዶላር ለአለም ባንክ ለመስጠት ቃል ገቡ
ፕሬዝዳንቱ ቃል የገቡት በብራዚል እየተካሄደ በሚገኘው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ ነው
የዘንድሮው ጉባኤ በ2030 600 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን ከድህነት ለማውጣት ስትራቴጂ የሚነደፍበት ነው ተብሏል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለአለም ባንክ በአለም አቀፍ ልማት ትብብር ፈንድ በኩል ለድሀ ሀገራት የሚከፋፈል 4 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ቃል መግባታቸው ተነግሯል፡፡
በብራዚል ሪዮዲጂኔሮ እየተካሄደ በሚገኘው የዘንድሮ የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከሌሎች የአለም መሪዎች ጋር እየመከሩ የሚገኙት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ድህነት ቅነሳ እና ርሀብን ማስወገድ ላይ አባላቱ በቅርበት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
ገንዘቡ በሶስት አመታት ውስጥ የሚለቀቅ ሲሆን በተለይም መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ፣ የአየር ንብረትን መቋቋም የሚችል የግብርና ስርአትን ለማስተዋወቅ እና ድሀነትን ለመቀነስ እንደሚውል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በጉባኤው ላይ አሜሪካ ቃል የገባቸው በአለም ባንክ በኩል ለአለም አቀፍ ትብብር ፈንድ (አይዲኤ) ይሰጣል የተባለው ገንዘብ ዋሽንግተን በ2021 ለመስጠት ቃልገብታው ከነበረው 3.5 ቢሊየን ዶላር ጋር ሲንጻጸር በአይነቱ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡
የውጭ የገንዘብ ድጋፎችን ለማቋረጥ ቃል ከመግባት አልፈው የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ ለቢሊየነሩ ኢለን መስክ የመንግስት ስልጣን የሰጡት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን የባይደን ቃል እንደሚጠብቁ የታወቀ ነገር የለም፡፡
በብራዚሉ ጉባኤ ባይደን ለአለም አቀፍ ትብብር ፈንድ አዲስ ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸውን የፕሬዝዳንቱ ምክትል የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጆናታን ፊነር ተናግረው ነበር፡፡
አማካሪው አክለውም ከብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ጋር በነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይት የታዳሽ ሀይልን ምርት ለማጠከር የአጋርነት ስምምነት ለመፈጸም ተስማምተዋል ብለዋል፡፡
በዋነኛነት ለድሀ ሀገራት በዝቅተኛ ወለድ ብድር እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው የአለም ባንክ “አይዲኤ ፈንድ” በየሶስት አመቱ የሚደርገውን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንፈረንስ ከታህሳስ 5-6 በደቡብ ኮርያ ሴኡል ለማካሄድ ቀጠሮ ይዟል።
የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ በአፍሪካ እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ድሀ ሀገራት ከዕዳ ጫና ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች፣ ከግጭት እና ከሌሎች ጫናዎች ጋር እየታገሉ ባሉበት ወቅት በ2021 ተስብስቦ ከነበረው የ93 ቢሊየን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዚህ አመት እስከ 120 ቢሊየን ዶላር ማሰባሰብ እንደሚቻል ተናግረው ይህን ለማሳከት ግን ሀገራት የድጋፍ ቁርጠኛነታቸው ላይ ጥያቄ ሊኖር አይገባም ነው ያሉት፡፡
አዲሱ የአሜሪካ የድጋፍ ቃልኪዳን በ2021 ከተደረገው ድጋፍ በ14.3 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡
በተመሳሳይ በጥቅምት ወር በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤም ኤፍ) እና የዓለም ባንክ አመታዊ ስብሰባዎች ላይ ስፔን የምታደርገውን ድጋፍ በ 37 በመቶ በማሳደግ 423 ሚሊዮን ዶላር ፣ ዴንማርክ በበኩሏ 492 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
600 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን ከርሀብ ለማውጣት ስትራቴጂ ይነደፍበታል የተባለው የዘንድሮ የቡድን 20 አባል ሀገራት አመታዊ ጉባኤ ከትላንት ጀምሮ በብራዚል አስተናጋጅነት እየተካሄደ ነው፡፡