ለረጅም ሰአት ቁጭ ብሎ ማሳለፍ የልብ ህመምን እንደሚያስከትል አዲስ ጥናት አመላከተ
የልብ ድካም ፣ ስትሮክ ፣ የደም ስር በሽታ እና የልብ ስራ ማቆም ከመቀመጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በሽታዎች ናቸው
በቢሮ ውስጥ እና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ብዙ ጊዜያቸውን ቁጭ ብለው የሚያሳልፉ ሰዎች ከረፈደ በኋላ የሚያደርጉት የስፖርት እንቅስቃሴ ከበሽታ አይታደጋቸውም ተብሏል
ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብለው የሚያሳልፉ ሰዎች ለልብ ህመም በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ መሆናቸውን አዲስ የጥናት ግኝት አረጋገጠ፡፡
የቢሮ ሰራተኞችን ጨምሮ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች እና ሌሎች የስራ ዘርፎች ከስራ ባህርያቸው ጋር በተያያዘ የቀናቸውን አብዘሀኛውን ክፍል ተቀምጠው ያሳልፋሉ፡፡
በቦስተን ሆስፒታል የመተንፈሻ አካላት ሃኪም ዶክተር ኢዚም አጁፎ ሰዎች ለረጅም ጊዜ መቀመጠን ማስወገድ እንደሚኖርባቸው አዲስ የተደረገው የጥናት ውጤት እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ የ90 ሺህ ሰዎችን የህይወት ዘየ እና አዋዋል አስመልክቶ በሰበሰቡት መረጃ የቀናቸውን በርካታ ክፍል በመቀመጥ የሚያሳልፉ ሰዎች በኋለኛው ዘመናቸው ስትሮክ ፣ የልብ ድካም እና የልብ ስራ ማቆም አደጋ ሊከሰትባቸው እንደሚችል በግኝታቸው አረጋግጠዋል፡፡
በዚህም እነኚህ ሰዎች ለልብና የደም ስር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው በእንቅስቃሴ ውስጥ ከሚያሳልፉ ሰዎች በበለጠ እጅግ የጨመረ መሆኑ ሲገለጽ፤ ተቀምጠው የሚውሉ ሰዎች በትርፍ ጊዜያቸው የስፖርት እንቅስቃሴ እንኳን ቢያደርጉ ለበሽታ የመጋለጥ እድላቸው ላይ እምብዛም ለውጥ እንደማይኖረው ተነግሯል፡፡
ከተመራማሪዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት በቦስተን ሆስፒታል የመተንፈሻ አካላት ሃኪም ኢዚም አጁፎ በተቻለ መጠን ሰዎች በቀን ከ10.6 ሰአታት በላይ እንዳይቀመጡ መክረዋል፡፡
ጡንቻዎች በደም ውስጥ ያለውን የስኳር እና የስብ መጠን ለመቆጣጠር በጣም ጠቃሚ ናቸው ያሉት ተመራማሪው ይህን ስራቸውን ደግሞ በደንብ ለመስራት ጡንቻዎች እንቅስቃሴ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከስራ ባህርያቸው አንጻር እና በተለያየ ምክንያት ለረጅም ሰአታት የሚቀመጡ ሰዎች በቀናቸው አጋማሽ ላይ ለመንቀሳቀስ የተወሰነ እረፍትን መውሰድ ማስለመድ እንደሚኖርባቸው ነው የተነገረው፡፡
ጡንቻዎች ስኳርን እና ቅባቶችን በብቃት የሚብላሉበትን ጊዜ ለመስጠት በተወሰነ ሰአት ልዩነት በደረጃዎች ላይ መንቀሳቀስ ፣ ብስክሌት መጠቀም ፣ በእግር የአጭር ርቀት ጉዞ ማድረግ አደጋዎች ሊቀለበሱ በማይችሉበት ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ለመከላከል ያስችላሉ፡፡
እነዚህን እንቅስቃሴዎች በግማሽ ሰአት ልዩነት ወይም አንድ ስራ ጨርሰው ወደሌሎች ስራዎች ከመሸጋገር በፊት መተግበር ጠቃሚ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡
ይህ ካልሆነ ለረጅም ጊዜ በተደጋጋመ ልምድ የሚመጡ በሽታዎች ከተከሰቱ በኋላ በስፖርት እንቅስቃሴ ለማጥፋት ወይም ለማስወገድ የሚደረገው ጥረትም እንደማይሰራ በሲኤንኤን ዘገባ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በጥናቱ ውስጥ ያልተሳተፉት በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ኪት ዲያዝ አብዝቶ መቀመጥ ለጤና ጎጂ ሊሆን እንደሚችል አጠቃላይ ግንዛቤ ቢኖርም ትክክለኛ አደጋዎችን እና የጤና ጉዳቶችን ለመገንዘብ ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡