የአሜሪካ ሴኔት ለእስራኤል የሚደርገውን የጦር መሳርያ ሽያጭ በሚከለክለው ረቂቅ ህግ ላይ ድምጽ ሊሰጥ ነው
በነገው እለት ይካሄዳል የተባለው የድምጽ አሰጣጥ ከፍልስጤም ሰብአዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ የጦር መሳርያዎችን ሽያጭ ሊያግድ ይችላል
የውሳኔ ሀሳቡን ያዘጋጁት የሴኔት አባላት እስራኤል ንጹሀንን ከሀማስ ታጣቂዎች ለመለየት ያደረገችው ጥረት እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል
የአሜሪካ ሴኔት ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ሽያጭን የሚከለክል ረቂቅ ህግ ላይ ረቡዕ ድምጽ ይሰጣል፡፡
እስራኤል በጋዛ ለፍልስጤም ንጹሀን ዜጎች የሚደረገውን መሰረታዊ የሰብአዊ ድጋፍ ስርጭት አስተጓጉላለች ባሉ የሕግ አውጭዎች በተዘጋጀ ረቂቅ ላይ ነው ሴኔቱ ድምጽ የሚሰጠው።
በዚህ ረቂቅ ላይ የታንክ ተተኳሾን ጨምሮ ፣ 120 ሚሊሜትር የሞርታር ተተኳሾች እንዲሁም ሌሎች በተሸከርካሪዎች በሚገጠሙ እና በቡድን መሳርያዎች ተተኳሾ ሽያጭ ላይ ክልከላ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው፡፡
ከህጉ አዘጋጆች መካከል አንዱ የሆኑት በርኒ ሳንደርስ ይህ ጦርነት ከሞላ ጎደል የተካሄደው በአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች እና በ18 ቢሊዮን ዶላር የአሜሪካ ግብር ከፋይ ዶላር ነው ብለዋል።
ሴናተሩ ባደረጉት ንግግር “እስራኤል ከአሜሪካ የተሰጣትን 2 ሺህ ፓውንድ ክብደት ያላቸው ቦምቦች በተጨናነቁ የመኖርያ ሰፈሮች ውስጥ በመጣል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ገድላ ጥቂት የሐማስ ተዋጊዎች ላይ ጉዳት ማድረስ ችላለች፤ በእስካሁኑ ጦርነት ንጹሀን እና ተዋጊዎችን ለመለየት ያደረገችው ጥረትም ዝቅተኛ ነው” ብለዋል፡፡
የባይደን አስተዳደር በጥቅምት ወር እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባ የእርዳታ አቅርቦትን እንድታሻሻል ይህ ካልሆነ በጦር መሳርያ ድጋፍ ላይ እቀባ እንደሚያደርግ በማስጠንቀቅ የ30 ቀናት ቀነ ገደብ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከሳምንት በፊት ይህ ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ የእርዳታ ስርጭቱ መስተካከሉን ያወጀው አስተዳደሩ ለእስራኤል የሚያደርገውን ድጋፍ እንደማያቋርጥ ሲናገር የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው በስርጭቱ ዙርያ የተቀየሩ ሁኔታዎች አለመኖራቸውን በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡
ለሴኔቱ በነገው እለት የሚቀርበው የውሳኔ ሀሳብ በሴናተር በርኒ ሳንደርስ በገለልተኛ እና በዴሞክራት አባላት የተዘጋጀ ነው፡፡
ምንም እንኳን ሴኔቱ ህጉን ይጸድቃል ተብሎ ባይጠበቅም የጆ ባይደን አስተዳደር እና የእስራኤል መንግስት ንጹሀንን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ላይ ማሻሻያዎችን ኢንዲያደርጉ ያስችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
2.3 ሚሊዮን ህዝብ በሚገኝበት ጋዛ ከ1.9 ሚሊየን የሚሻገሩት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው የረሀብ አደጋ የተጋረጠ ሲሆን 13 ወራትን በፈጀው የእስራኤል ጥቃት ወደ 44 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን የጋዛ ጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ህግ ኮንግረሱ የተቃውሞ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዋና ዋና የውጭ የጦር መሳሪያ ሽያጮችን የማስቆም መብት ይሰጣል።
ምንም እንኳን እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች በኮንግረስ እና ሴኔቱ ተቀባይነት የማግኘት እድል ጠባብ ቢሆንም፤ ከዚህ ቢያልፉም ከፕሬዚዳንቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የሚተርፉ ባይሆኑም ህጉ የውሳኔ ሀሳብ ሆኖ ከቀረበ ሴኔቱ ድምጽ እንዲሰጥ ያስገድዳል።