ፕሬዝዳንት ባይደን ለዩክሬን ተጨማሪ የ800 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ እሰጣለሁ ብለዋል
አሜሪካ ዓለምን ለመምራት በተሻለ ቁመና ላይ መሆኗን ገለጸች፡፡
የሩሲያ ጦር ወደ ዩክሬን ገብቶ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ነበር ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ወይም ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡት፡፡
ሁለቱ የሩሲያ ጎረቤት ሀገራት ኔቶን እንቀላቀል ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው አሜሪካ አሁን ላይ ዓለምን ለመምራት ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት በተሻለ ቁመና ላይ እንደምትገኝ ተናግረው ሩሲያን የማዳከሙ ስራ እንደሚቀጥል አክለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የሩሲያ ጎረቤት የሆኑት እና የኔቶ አባል ያልነበሩት ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን መቀላቀላቸው ለአሜሪካ እና ምዕራቡ ዓለም ትልቅ ስኬት ነው ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ከዚህ በፊት የኔቶ አባል ሀገራት ከሩሲያ ድንበር ጋር የነበራቸውን ርቀት በማሳነስ በ800 ማይል ርቀት ላይ ብቻ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡
ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬንም ተጨማሪ የ800 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጹት ፕሬዝዳንት ባይደን በአጠቃላይ ሀገራቸው ለዩክሬን 7 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ተደርጎላታል፡፡
የአሁኑ የጦር መሳሪያ ከሩሲያ የሚሰነዘሩ የአየር ላይ ጥቃቶችን መመከት የሚያስችል ዘመናዊ የአየር ክልል መከላከያ መሳሪያን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን እንዳካተተ ተገልጿል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ከዚህ በፊት 30 ዓባላት ያሉት ሲሆን ስዊድን እና ፊንላንድ ሲጨመሩ 32 ኣባላትን በመያዝ የጦር መጠኑንም ወደ 300 ሺህ እና ከዛ በላይ የማድረግ ውጥን አለው ተብሏል፡፡
ኔቶ ዓመታዊ ጉባኤውን በስፔን መዲና ማድሪድ በማካሄድ ላይ ሲሆን ለዩክሬን የተለየ ድጋፍ በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ አዳዲስ ውሳኔዎችን እንደሚወስን ይጠበቃል፡፡