ኢኮኖሚ
የሰሜን ኮሪያ መንታፊዎች ከአሜሪካ 100 ሚሊዮን ዶላር መመዝበራቸው ተገለጸ
የበይነ መረብ መርማሪዎች እንዳረጋገጡት ከሆነ የሰሜን ኮሪያ መንታፊዎች ገንዘቡን መዝብረዋል ተብሏል
ምዝበራውን ተከትሎ የድጅታል መገበያያ ገንዘቦች ዋጋ የ20 ሺህ ዶላር ቅናሽ ማሳየቱ ተገልጿል
የሰሜን ኮሪያ መንታፊዎች ከአንድ የአሜሪካ ኩባንያ 100 ሚሊዮን ዶላር መመዝበራቸው ተገለጸ፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ አንድ የአሜሪካ ኩባንያ በሰሜን ኮሪያ የበይነ መረብ ጠላፊዎች ባደረሱት ጥቃት ምክንያት 100 ሚሊን ዶላር ተመዝብሯል፡፡
ምንተፋውን ተከትሎም የዓለም ድጅታል መገበያያ ገንዘቦች ዕለታዊ የመሸጫ ዋጋ በአማካኝ የ1 በመቶ ወይም የ20 ሺህ ዶላር ቅናሽ እንዳሳየም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በተለይም ኢቴረም የተሰኘው የድጅታል መገበያያ ገንዘብ ከምዝበራው በኋላ የ5 በመቶ ወይም የአንድ ሺህ ዶላር ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ በይነ መረብ ጥቃት መርማሪዎች እንዳረጋገጡት ከሆነ ድርጊቱን የሰሜን ኮሪያ ጠላፊዎች እንደፈጸሙት ተገልጿል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ከዚህ በፊት ባወጣው ሪፖርት ሰሜን ኮሪያ ከተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ላይ የበይነ መረብ መንታፊዎቿን በመጠቀም እና ከዚህ በምታገኘው ገንዘብ የኑክሌር አረሮችን እያለማች ነው ሲል መክሰሱ ይታወሳል፡፡
ሰሜን ኮሪያ የተመድን ክስ ብታስተባብልም በመንግስት የሚደገፍ የበይነ መረብ ምዝበራን የሚፈጽሙ ባለሙያዎችን በየጊዜው እያሰለጠነች እንደምትገኝ በተደጋጋሚ በምዕራባዊያን ይገለጻል፡፡