"የዩክሬን ወታደሮች ጦር አውርደው ያስቀመጥኳቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ሲቀበሉ ብቻ ጦርነቱ ያበቃል" - ሩሲያ
ዜሌንስኪ ጦርነቱ የተያዘው የፈረንጆች ዓመት ከማለቁ በፊት እንዲያበቃ ግፊት እንዲያደርጉ ምዕራባውያንን መጠየቃቸው ይታወሳል
"የዩክሬን ወገኖች ዛሬ ከማለቁ በፊት ሁሉንም ነገር ማቆም ይችላሉ" - ዲሚትሪ ፔስኮቭ
ጦርነቱ የሚቆመው የዩክሬን ወታደሮች ጦር አውርደው ያስቀመጠቻቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ሲቀበሉ ብቻ እንደሆነ ሩሲያ አስታወቀች፡፡
ኪቭ ወታደሮቿ ጦር እንዲያወርዱ አድርጋ ቅድመ ሁኔታዎቹን በተቀበለች ጊዜ ጦርነቱ ሊቆም እንደሚችል የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጽህፈት ቤት ትናንት ማክሰኞ አስታውቋል፡፡
ሁኔታዎችን በማስመልከት ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "የዩክሬን ወገኖች ዛሬ ከማለቁ በፊት ሁሉንም ነገር ማቆም ይችላሉ" ብለዋል፡፡
ሆኖም ኪቭ የሞስኮን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ግድ እንደሚላት ገልጸው ወታደሮቿ ጦር እንዲያወርዱ ማዘዙም አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል ፔስኮቭ፡፡
ወደ ኪቭ ታደርግ የነበረውን ግስጋሴ ወደ ምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል ያደረገችው ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ናት፡፡ በቅርቡ ሴቬሮዶኔስክ የተባለችውን የኢንዱስትሪ ከተማ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋሏም ይታወሳል፡፡
ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን ዶንባስ ግዛት የሚገኙትን የሉሃንስክ እና የዶኔስክ አካባቢዎችን ራስ ገዝ አድርጋ ነጻ የማውጣት ውጥንም አላት፡፡
ይህ የተጠናከረ የሩሲያ ዘመቻ ስጋት ያሳደረባቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጦርነቱ የተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከማለቁ በፊት የሚያበቃበትን መላ እንዲዘይድ ጠይቀዋል፡፡
ጫና ከማድረግ በዘለለ የጀመሩትን የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው በቡድን 7 አባል ሃገራት ጉባዔ ላይ የተናገሩት፡፡
በጉባዔው ሩሲያ ኪቭ በሚገኝ የገበያ አዳራሽ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ያወገዙት የቡድኑ አባላት ጥቃቱ በጦር ወንጀል የሚያጠይቅ ነው ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡