የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ባይደን ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በኮቪድ ተይዘው ነበር
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በኮቪድ 19 (ኮሮና ቫይረስ) መጠቃታቸውን ኋይት ሃውስ አስታወቀ።
ከዴሞክራቶች ራሳቸውን ከምርጫ እንዲያስወጡ ግፊት እየበረታባው የመጣው ፕሬዝዳንት ባይደን በትናንትናው እለት በላስ ቬጋስ ጉብኝት በማድረግ ላይ እያሉ ነው በኮቪድ መያዛቸው የታወቀው።
የ81 ዓመቱ ባይደን የኮቪድ ምርመራ አድርገው በቫይረሱ መያዛቸውን እና ቀለል ያሉ የህመሙን ምልክቶች እያሳዩ መሆኑም ተነግሯል፡፡
የኋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ዣን ፒየር፤ ፕሬዝዳንቱ በአሁኑ ወቅት መካከለኛ የሆነ የህመሙ ምልክቶች እንደታዩባቸው እና በዴልዋሬ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ራሳቸውን አግልለው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በዴልዋሬ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሆነው ሁሉንም ሃላፊነቶቻቸውን እንደሚወጡ የኋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከላስ ቬጋስ ወደ ዴልዋሬ በማቅናት ላይ እያሉ ለሪፖርተሮች በሰጡት ቃል፤ “ጠሩ ላይ ነኝ፤ አሁን ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ ነው” ብለዋል።
ሆኖም ግን አውሮፕን ላይ ሲሳፈሩ ደረጃውን ቀስ እያሉ እና በየመሃሉ እየቆሙ እና እያረፉ እንደነበረ ነው የተነገረው።
የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ባይደን ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በኮቪድ ተይዘው የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ቫይረሱ ሲገኝባቸው ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንት ባይደን የኮቪድ-19 ክትባት መውሰዳቸውም ይታወሳል።