ከምርጫ ራሳቸውን እንዲያገሉ ጫና የበረታባቸው ባይደን “የትም አልሄድም” አሉ
ባይደን ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ክርክር ያሳዩትን ደካማ አቋም ተከትሎ ከዴሞክራች ጫና በርትቶባቸዋል
ባይደን “የ90 ደቂቃ የመድረክ ላይ ድክመቴን ሳይሆን ባለፉት 3 ዓመታት የሰራሁትን መልካም ስራዎች ተመልከቱ” ብለዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እየበረታባቸው የመጣውን የድጋሚ የምርጫ ፉክክር የማቋረጥ ጥሪ “የትም አልሄድም” ሲሉ አጣጣሉ።
የ81 ዓመቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሪፐብሊካኑ ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር በቀጥታ ያደረጉትን ክርክር ተከትሎ ከአቋማቸው እና ከአእምሯቸው ጤነንት ጋር በተያያዘ ጫናዎች እየበረቱባው መጥተዋል።
ጆ ባይደን ባሳለፍነው ሳምንት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በቴሌቪዥን በቀጥታ ባደረጉት ክርክር ላይ ደካማ አፈጻጸም አሳይቷል ነው የተባለው።
ጆ ባይደን ድምጻቸው ደክሞ፣ በራስ መተማመናቸው ጠፍቶ፣ አቀርቅረው፣ ሃሳባቸው ተበትኖና አንደበታቸው ተሳስሮ ነበር ክርክሩን የጨረሱት።
ይህንን ተከትሎም የጆ ባይደን ፓርቲ የሆነው የዴሞክራት አባላት ፐሬዝዳንቱ በምርጫው ሊሸነፉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን በመግለጽ ራሳቸውን በይፋ ከምርጫው እንዲያገሉ ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
ጆ ባይደን በትናንትናው እለት በተከበረ የነጻነት ቀን ላይ “ትግሉን ቀጥሉ” የሚል መፈከር ላሰሙ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፤ የምርጫ ፉክክሩን የማቆም ፍላጎት እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
በዋይት ሃውስ በተካሄደ ዝግጅት ላይ ንግግር ያደረጉት ባይደን “ተረድታችሁኛል፤ እኔ ወደየትም አልሄድም” ብለዋል።
“ስህተት ሰርቻለሁ” ያሉት ባይደን፤ “የ90 ደቂቃ የመድረክ ላይ ድክመቴን ሳይሆን ባለፉት 3 ዓመታት የሰራሁትን መልካም ስራዎች ተመልከቱ” ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን የማግለል ፍላጎት ባይኖራቸውም፤ ፓርቲያቸው ዴሞክራት ግን በምርጫው የማሸነፍ እድል ላይኖራቸው ይችላል በሚል ተተኪ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህን ተከትሎ ሮይተርስ ዶናልድ ትራምፕን ሊገዳደር የሚችሉ እጩዎች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ? ሲል ጥናት አካሂዷል።
በጥናቱ የተሳተፉ አሜሪካዊያን መካከል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ሚሼል ኦባማ የተሻለ ድምጽ አግኝተዋል።
ከሚሼል ኦባማ በመቀጠል የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ በሁለተኝነት ሲጠቀሱ የካሊፎርኒያው ገዢ ጋቪን ኒውሶም ደግሞ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።