ስጋት የገባቸው ዴሞክራቶች ጆ ባይደንን ለመተካት እየመከሩ ነው ተባለ
በሀሙሱ የምርጫ ክርክር ላይ የነበራቸው አቋም ደካማ ነበር የሚሉ አካላት ፕሬዝዳንቱ በምርጫ መወዳደር የለባቸውም እያሉ ነው
የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ እና የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ኤድቶሪያል ቦርድ ባይደን ከሀላፊነት እንዲነሱ ጠይቀዋል
በሀሙሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክርክር ጆ ባይደን ባሳዩት አቋም የተጨነቁ ዴሞክራቶች ባይደንን ከእጩነት ለማንሳት እየመከሩ መሆኑ ተሰምቷል።
ሁለቱ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን ባደረጉት ተጠባቂ ክርክር የስደተኞች ጉዳይ ፣ ኢኮኖሚ ፣ የዩክሬን እና ጋዛ ጦርነት እንዲሁም በእጩዎቹ የመምራት አቅም ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር።
በክርክሩ ላይ ጉልበት ባነሰው በለሆሳስ ድምጽ ንግግር ሲያደርጉ የነበሩት ጆ ባይደን በትራምፕ ብልጫ እንደተወሰደባቸው ተነግሯል፡፡
ከክርክሩ በኋላ ሲኤንኤን ያሰባሰበው የህዝብ ድምጽ እንደሚያመላክተው 67 በመቶ የተመዘገቡ መራጮች ትራምፕ በክርክሩ እንዳሸነፉ ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ባይደን በስልጣን ለመቆየት በሚያስችል የጤና እና እድሜ ሁኔታ ላይ አይገኙም ያሉ አካላት ዴሞክራቶች የእጩ ለውጥ እንዲያደርጉ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ማይክ ጆንሰን ክርክሩ የ81 አመቱ ፕሬዝዳንት የሚገኙበት ሁኔታ ሀገሪቷን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በግልጽ ያሳየ ምሽት ብለውታል፡፡
የሪፐብሊክን ፓርቲ አባል የሆኑት ጆንሰን እኔ የዴሞክራት ፓርቲ አባል ብሆን ኖሮ ባይደን በሌለ እጩ እንዲተኩ ለማድረግ አላቅማማም ነበር ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ሰአት ዴሞክራቶች ባይደንን መተካት በሚኖረው ጠቀሜታ እና ኪሳራ ላይ እየመከሩ ሲሆን የፓርቲው ደጋፊዎች ወጣት እጩ እንዲያቀርቡ ጫና እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
ምርጫው ሊደረግ ከአራት ወራት ያነሱ ግዚያት በቀሩ ጊዜ አዲስ እጩ አስተዋውቆ እና በአዲስ መልክ የምርጫ ቅስቀሳ አድርጎ የማሸነፍ አድሎ ጠባብ ነው ያሉ የፓርቲው አባላት ጆ ባይደን እንዲቀጥሉ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
ዩጎቭ ፖል የተሰኝው የህዝብ አስተያየት የሚሰበስብ ተቋም ባሰባሰበው ድምጽ 49 በመቶ የዴሞክራት ፓርቲ ደጋፊዎች ባይደን በሌላ እጩ መተካት እንዳለባቸው 30 በመቶዎቹ ደግሞ በእጩነት እንዲቀጥሉ እንደሚሹ አስታውቋል፡፡
እንደ ቪኦኤ ዘገባ በአሁኑ ወቅት ዴሞክራቶች በዝግ ቤት በጉዳዩ ላይ እየመከሩ ይገኛሉ ሆኖም በሁለቱም አቅጣጫ የሚወስኑት ውሳኔ ትልቅ አደጋን መጋፈጥ የሚያመጣ ነው፡፡
ባይደን በእጩነት የሚቀጥሉ ከሆነ ሀሙስ የነበራቸውን አፈጻጸም አይተው መቀየራቸውን የሻቱ ዴሞክራቶችን ድምጽ ፓርቲው ሊያጣ ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ባይደንን በሌላ እጩ የሚተካ ከሆነ እስከዛሬ ፓርቲው ያከናወናቸው የምርጫ ቅስቀሳዎች እና ገንዘብ ማሰባሰቦችን በሙሉ ከአዲስ መጀመር ይኖርበታል፡፡