ጆ ባይደን በፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመጀመሪያ ንግግራቸውን አድርገዋል
በፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጀት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመጀመሪያ ንግግራቸውን ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሀገራቸው አዲስ የቀዝቃው ጦርነት እንደማትፈልግ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በንግግራቸው ዓለም ላይ የተደቀኑ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ እና ለማሸነፍ ዋሸንግተን ከቀሪው ዓለም ጋር ተባብራ መሥራት እንዳለባት ገልጸዋል። ሀገራቸው በቀጣይ የቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላታም ጆ ባይደን ገልጸዋል።
- ፕሬዝዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ማእቀብ እንዲጣል ትእዛዝ አስተላለፉ
- “የአፍጋኒስታን ተልዕኳችን ሃገሪቱን ለመገንባት አልነበረም”- ጆ ባይደን፣ አሜሪካ ፕሬዝዳንት
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ይበሉ እንጅ ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት ለመግባት ተደረገ የተባለ ሙከራም ሆነ ወደዚህ ሊገቡ ነው ያሏቸውን ሀገራት ስም አልጠቀሱም።
አሜሪካ ውድድሯን እንደምትቀጥል ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በጥንካሬዎቿ እና በእሴቷ ግን መምራቷን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን አሜሪካ ከአጋሮቿ ጎን እንደምትቆም የገለጹ ሲሆን “ጠንካራ” ሀገራት “ደካማ” የሚባሉትን እንዳይቆጣጠሩ እና እንዳይጫኑ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርጉና እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።
ዓለም ወግ አጥባቂ ወደ ሆኑ ክፍፍሎች (ብሎኮች) እንዲገባ እንደማይፈልጉም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።
ባይደን በ20 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያ ንግግራቸውን በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ያደረጉት አሜሪካ ከጦርነት ውጭ ሆና እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከጉባዔው መክፈቻ ቀደም ብለው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር ተገናኝተው ነበር።
ሁለቱ ወገኖች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፤ በአየር ንብረት ለውጥ፤ እንዲሁም በየጊዜው እየጨመረ በመጣው የአሜሪካና የቻይና ግንኙነት መሻከር ላይ መምከራቸው ተሰምቷል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ ዋሸንግተን እና ቤጅንግ ያላቸውን ግንኙነት መጠገን እንዳለባቸው ሃሳብ ማቅረባቸው ተሰምቷል።