ፕሬዝዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ማእቀብ እንዲጣል ትእዛዝ አስተላለፉ
ማዕቀቡ በኢትዮጵያ፣በኤረትራ መንግስት፣ በአማራ ክልል መስተዳደርና በህወሓት አመራሮች ላይ የሚያነጣጥር ነው
በማእቀቡ በኢትዮጵያ ግጭት ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦች በአሜሪካ ያላቸውን ሀብታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ እግድ ተጥሏል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ከሚሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በግለሰቦች ላይ ማእቀብ መጣል የሚያስችል ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ፤ የአሜሪካ ግምጃ ቤት በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ ተሳትፈዋል ብሎ በሚያምናቸው ግለሰቦች ላይ ማእቀብ እንዲጣል በፊርማቸው ማዘዛቸውን ኃይት ሃውስ በወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳት ባይደን ማእቀቡን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ፤ በሰሜን እትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሰብአዊ ድጋፍ እንዲፈልጉ እና ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
ለግጭቱ ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች ላይ የሚደረገው ጫና እንዳለ ሆኖ የአሜሪካ መንግስት ለችግር የተጋለጡ ሰዎች የሚሆኑ አስፈላጊ ድጋፎች መንግስትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች አማካኝነት ያለ ምንም እንቅፋት እንዲደርሱ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
በስምምነት ላይ የተመሰረት የተኩስ አቁም እንዲደረስ፣ አሁን ላለው ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲመጣ፣ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ግዛት ለቆ እንዲወጣ እና አንድነቷ የተጠበቀ እና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት እንደሚደግፈውም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባለው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት ውስጥ፣ እንዲሁም በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በሙስና እና በሰብአዊ ጥሰት ተግባራት፣ የሰብአዊ ድጋፎች ለተጎጂዎች እንዳይደረሱ እንቅፋት በሚሆኑ፣ ተኩስ አቁም ላይ ለመድረስ አሊያም የሚካሄዱ ሰላምን የማምጣት ሂደቶች በማደነቀፍ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ ላይ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ማእቀብ እንዲጥል ትእዛዝ ማስተላፋቸውንም አስታውቀዋል።
ማዕቀቡ ከላይ ለተጠቀሱት ጉዳዮች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ የኢትዮጵያ መንግስት እና የአማራ ክልል መስተዳደር ባለስልጣናት እንዲሁም በህወሓትና በኤርትራ መንግስት አመራሮች ላይ የሚጣል እንደሆነ አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የመንግስት ግምጃቤት ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመሆን ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውን እየለየ ማዕቀቡን ተግባራዊ ኢንዲያድርግ ኃላፊነት እንደተሰጠውም አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት ተጠያቂ የሚደረጉ ግለሰቦች ላይ የአሜሪካ ግምጃ ቤት በአሜሪካ ውስጥ ያላቸውን ንብረት ከማገድ ጀምሮ ከአሜሪካ ዜጎች ጋርም ሆነ ተቋማት ጋር ምንመ አይነት የኢንቨስትመንት ግንኙነት የብድር እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዳያገኙ መከልከል የይገኝበታል።
በተጨማሪም ወደ ተጠያቂ የሚደረጉ ግለሰቦች እና የንግድ አጋሮቻቸው የጉዞ እና የገንዘብ እንቅስቃሴ እገዳ በውስጡ አካቷል።
አሜሪካ እንዳይገቡ ቪዛ መከልከልን፣ የመኖሪያ ፍዳቅ መከልከል እና ማገድን ጨመሮ በርካታ ማእቀቦችን በውስጡ አካቷል።
መግለጫው በግጭቱ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስት የመንግስት ባለስልጣናት እና የህወሓት አመራሮች ማንነት ግን ይፋ አላደረገም።
ማዕቀቡ የኢትዮጵያ ህዝብን በማይጎዳ መልኩ በተመረጡ ግለሰቦች ላይ ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግም ኋይት ዋይት ሀውስ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ እገዳ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን፤ ጉዞ እገዳው የተጣለባቸው እነማን ናቸው የሚለውን ግን እስካሁን አላስታወቀም።
አሜሪካ ባሳለፍነው ወር የኤርትራ ጦር በትግራይ ክልል ፈጽሟል ባለችው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት በኤርትራ ጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሀንስ ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።