“የአፍጋኒስታን ተልዕኳችን ሃገሪቱን ለመገንባት አልነበረም”- ጆ ባይደን፣ አሜሪካ ፕሬዝዳንት
ጀርመን የምዕራባውያን ወታደሮች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸው ኔቶ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያጋጠመው “ትልቁ ውድቀት” ነው ስትል ገልጻለች
ባይደን አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ወታደሮቿን ማስወጣቷ ትክክለኛ እና የማይጸጸቱበት እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ወታደሮቿን ማስወጣቷ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ታሊባን የአፍጋኒስታንን ዋና ከተማ ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ንግግር አድርገዋል፡፡ ጆ ባይደን በንግግራቸው አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ አፍጋኒስታን ልካ የነበረው ሀገሪቱን ለመገንባት እንዳልነበረም ገልጸዋል፡፡ ታሊባን አፍጋኒስታንን የተቆጣጠረበት መንገድ “ካወቅነው በበለጠ ፈጣን” እንደነበረም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ወታደሮችን ከአፍጋኒስታን ማስወጣት ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ ያነሱት ባይደን፤ ወታደሮቻቸው ከዚህ በኋላ መዋጋት እና መሞት እንደሌለባቸውም አንስተዋል፡፡ በውሳኔያቸው እንደማይጸጸቱም ነው የገለጹት፡፡
“የአፍጋኒስታን ወታደሮች ለራሳቸው መዋጋት ካልፈለጉ የአሜሪካ ወታደሮች ሊዋጉ እና ሊሞቱ አይችሉም” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ የአፍጋኒስታንን ወታደሮች ተችተዋል፡፡
ጆ ባይደን፤ የሀገሪቱ መንግስት መሪዎች ሀገር መልቀቃቸው እና ጦሩ መፍረሱ ከተጠበቀው በፈጠነ መንገድ መሄዱን ያነሱ ሲሆን ፤ የአፍጋኒስታን አመራርም ተስፋ ቆርጦ እንደነበር አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ በአፍጋኒስታንን ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ የተለያዩ ሀገራት አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
ጀርመን የምዕራባውያን ወታደሮች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያጋጠመው “ትልቁ ውድቀት” ነው ስትል ገልጻለች፡፡
መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል እና ምናልባትም ቀጣዩ የጀርመን መራሔ መንግስት ለመሆን ትልቅ ግምት የተሰጣቸው የመሪው ወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) ፓርቲ ሊቀመንበር አርሚን ላሼት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በአፍጋኒስታን የነበረው የተሳካ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ በአፍጋኒስታን ስጋት ላይ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገሯ እንደምታስገባም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ልዩ የኢሚግሬሽን ቪዛ በማዘጋጀት የአፍጋኒስታንን ጦር በማገዝ ላይ የነበሩ ዜጎችን እና ደህንነት የማይሰማቸውን ወደ አሜሪካ ለማምጣት ዋሸንግተን ቁርጠኛ መሆኗን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጭዎች፤ ከአሜሪካ ጋር ሲሰሩ የነበሩ አፍጋኒስታናውያን በታሊባን ጥቃት ሊደርስባቸው ስለሚችል ቶሎ ብለው ሀገሪቱን መልቀቅ እንዳለባቸው እየገለጹ ነው፡፡ ታሊባን ካቡል ከመግባቱ በፊት ከ34 የሀገሪቱ ግዛቶች 26 በቁጥጥሩ ስር ማዋሉ ተገልጿል፡፡