የአሜሪካና የሩሲያ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በስዊዘርላንድ ተገናኝተዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ለመጀመሪያ ጊዜ በስዊዘርላንድ ተገናኙ፡፡
ፕሬዝዳንቶቹን የስዊዘርላንዱፕሬዝዳንት ገይ ፓርሜሊን የተቀበሏቸው ሲሆን፤ የተሳካ የውይይት ጊዜ እንዲኖራቸውም ተመኝተውላቸዋል ነው የተባለው፡፡ ፑቲን እና ባይደን ፤ የሞስኮ እና የዋሸንግተን ግንኙነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፤ የአሜሪካው አቻቸው በአካል ለመገኛኘት ተነሳሽነት ማሳየታቸውን አድንቀዋል ነው የተባለው፡፡ ቭላድሚር ፑቲን፤ ከአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን ጋር ውይይታቸውም ፍሬያማ እንደሚሆን በአስተርጓሚያቸው በኩል መግለጻቸውን የአሜሪካ ድምጽ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ዘግቧል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው፤ የሩሲያ አቻቸውን አመስግነው ሁልጊዜም ቢሆን በአካል መገናኘት የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል ተብሏል፡፡ መሪዎቹ፤ ሀገሮቻቸው በትብብር በሚሰሩበት መንገድ ላይ ትኩረት አድረገው መወያየታቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና በሞስኮ እና ዋሸንግተን መካከል የነበሩ እሰጥ አገባዎችን መፍታትን በሚመለከት ፕሬዝዳንቶቹ ይህ ነው የሚባል ነገር አለመነጋገራቸውም ነው የተገለጸው፡፡ ሁለቱ መሪዎች የየሀገሮቻቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶችን ከማድረግ ይልቅ ቅሬታዎች ላይ ማተኮራቸው ነው የተነገረው፡፡
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ከዚህ ውይይት ብዙ ነገር እንደማይጠበቅ ቀደም ብለው መናራቸውንም የአሜሪካ ድምጽ ጽፏል፡፡