የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባይደን በአፍሪካ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
ባይደን ከ2005 ወዲህ ከሰሀራ በታች ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ይሆናሉ
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን የአፍሪካ ጉብኝት በቀጣይ ጥቅምት ወር ሊያካሄዱ መሆኑን ኃይት ሀውስ አስታውቋል
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባይደን በአፍሪካ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን የአፍሪካ ጉብኝት በቀጣይ ጥቅምት ወር ሊያካሄዱ መሆኑን ኃይት ሀውስ በትናንትናው እለት አስታውቋል።
ኃይት ሀውስ እንደገለጸው በጥቅምት ወር አጋማሽ ባይደን ደቡብ አፍሪካዊቷን አንጎላን እና አውሮፓዊቷን ጀርመንን ይጎበኛሉ።
ባይደን በ2022 መጨረሻ በዋሽንግተን በተካሄደው የአፍሪካ መሪዎችን ስብሰባ ወቅት አፍሪካን እንደሚጎበኙ ቃል ገብተው ነበር። ባይደን ጉብኝቱን የሚያደርጉት ከአህጉሪቷ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እና በከፊል ደግሞ እያደገ የመጣውን ዋነኛ የአሜሪካ ተቀናቃኝ የሆነችውን ቻይናን ተጽዕኖን ለመመከት ነው።
በርካታ የካቢኔ አባላት፣ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሀሪስ እንዲሁም ቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደን በ2023 የአፍሪካ ሀገራት ጎብኝተዋል፤ ነገርግን ባይደን ጉብኝት ሳያደርጉ በርካታ አመታት አልፈዋል።
የስልጣን ዘመናቸው ሊጠናቀቅ ጥቂት ወራት ብቻ የቀራቸው ባይደን ከጥቅምት 10-15 በርሊንን እና ሉዋንዳን ለመጎብኘት ማቀዳቸውን የኃይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሪን ጂን ፒሬ ተናግረዋል። ፕሬዝደንት ባይደን በተመድ ጉባኤ ላይ የመጨረሻ ንግግራቸውን ለማድረግ በኒው ዮርክ ይገኛሉ።
ባይደን ከ2005 ወዲህ ከሰሀራ በታች ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ይሆናሉ።
ፕሬዝደንቱ በጀርመን በርሊን በሚያደርጉት ስብሰባ ትብብር እንደሚያጠናክሩ እና ጀርመን ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን ለምታደርገው ድጋፍ አድናቆታቸውን እንደሚገልጹ ጂን ፔሪ ገልጸዋል።
ጂን ፔሪ አክለው እንደገለጹት ባይደን በአንጎላ ሉዋንዳ በሚኖራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ጃኦ ሎሪንኮ ጋር በአንጎላዋን ሎቢቶ ተጀምሮ አትላንቲክ ውቅያኖስን ከህንድ ወቅያኖስ የሚያገናኘውን የባቡር ፕሮጀክት ጨምሮ በተለያዩ መሰረተልማቶች እና በኢኮኖሚያዊ ትብብር ጉዳይ ይመክራሉ።