የኢራን መረጃ ጠላፊዎች የትራምፕን የምርጫ ዘመቻ መረጃ ለተቀናቃኛቸው ባይደን ማቀበላቸው ተሰማ
የመረት ጠላፊዎች የተለያዩ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሀን ጭምር በድብቅ አሳልፈው እንደሚሰጡ ተደርሶበታል
ኢራን፣ ሩስያ እና ቻይና በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ጣልቃ ለመግባት እየሞከሩ ነው በሚል አሜሪካ በተደጋጋሚ ትከሳለች
የኢራን የመረጃ ጠላፊዎች የዶናልድ ትራምፕን የምርጫ ዘመቻ መረጃዎችን በመጥለፍ ለጆ ባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድን አባላት ያስተላልፉ እንደነበር አሜሪካ ተናገረች፡፡
የመረጃ ጠላፊዎቹ የተለያዩ የምርጫ ዘመቻ እቅዶችን፣ ንግግሮችን እና አጀንዳዎችን ጭምር በመጥለፍ መረጃዎችን በኢሜል ያሰራጩ እንደነበር ተደርሶባቸዋል ነው የተባለው፡፡
የአሜሪካ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) እና የደህንነት ተቋማት በጋራ ባደረጉት ምርመራ ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን ከማግለላቸው በፊት የተቀናቃኛቸው መረጃዎች ለዘመቻ ቡድናቸው ይደርስ እንደነበር ነው ይፋ ያደረጉት፡፡
ኤፍቢአይ ባለፉት ወራት ኢራን ያሰማራቻቸው የመረጃ ጠላፊዎች ለህዝብ ይፋ መደረግ የሌለባቸውን መረጃዎች ለመገናኛ ብዙሀንም ይልኩ እንደነበር አስታውቋል፡፡
መረጃውን የተቀበሉት አካላት ከጠላፊዎቹ ለደረሳቸው መረጃዎች ምላሽ ስለመስጠት እና አለመስጠታቸው እንዲሁም መረጃውን ለትንተና እና ለተለያዩ ጉዳዮች ጥቅም ላይ ስለማዋላቸው የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡
ካሳለፍነው ሰኔ ወር ጀምሮ ኢራን በዴሞክራት እና ሪፐብሊካን እጩዎች የምርጫ ዘመቻ ሂደቶችን መረጃ ለመመንተፍ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲታደርግ እንደነበር ዋሽንግተን ስትከስ ቆይታለች፡፡
የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቃልአቀባይ ካሮሊን ሌቪት ይህ በግልጽ የኢራን አገዛዝ በምርጫ ጣልቃ እየገባ እንደሚገኝ እና የባይደን እና የካማላ አስተዳደር እንዲያሸንፍ እያገዘ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
“ይህን የሚያደርጉበት ምክንያትም ትራምፕ ከተመረጡ ሽብርተኝነትን በመደገፍ እያደረሱ ለሚገኙት ጥፋት ከፍተኛ ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው ስለሚያውቁ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድን ምን አይነት መረጃ እንደደረሰው እና መረጃውን የት እንዳደረሰው ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡
የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምርመራውን የቀጠለ ሲሆን የግል መረጃቸው ተጠልፏል የተባሉትን አካላት የኤሌክትሮኒክስ ፍተሻ እና ደህንነት ማጠናከር ላይ እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ዋሽንግተን ቻይና ፣ ሩስያ እና ኢራን በዘንድሮው ምርጫ ጣልቃ ለመግባት የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ ትከሳለች፡፡
ማህበራዊ ትስስር ገጾችን እና ሰውሰራሽ አስተውሎቶችን ጭምር ይጠቀማል የሚባለው የምርጫ ጣልቃገብነት የመራጮችን አዕምሮ የመቆጣጠር እና ተጽእኖ መፍጠርን ያካትታል፡፡
ለዚህ ደግሞ በርካታ ሰዎች በሚጠቀሟቸው የማህበራዊ ትስስር ገጾች በሀሰተኛ ስም የሚከፈቱ በርካታ ገጾች እንዳሉ ተነግሯል፡፡