ጥቂት ባለጸጎች በአሜሪካ ዴሞክራሲ ላይ ስጋት ደቅነዋል- ባይደን
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባደረጉት የስንብት ህዝባዊ ንግግር አሜሪካውያን ሀገራችውን ነቅተው እንዲጠብቁ አደራ ብለዋል
ፕሬዝዳንቱ በእጃቸው ላይ ከፍተኛ ሀይል እንደሚገኝ ገልጸው በስጋትነት የሳሏቸውን አካላት ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለጸጎች እና ጥቂት ሀያላን በመንግስት ስልጣን ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣት ለአሜሪካ ዴሞክራሲ ስጋት መደቀኑን ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ የአስርት አመታት የፖለቲካ ጉዟቸው መቋጫ ላይ በሚገኙበት ጊዜ በኋይት ሀውስ ለህዝብ ባደረጉት የመሰናበቻ ንግግር መጪው ጊዜ እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ሀብት ፣ ስልጣን እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በጥቂቶች እጅ መውደቁ የሀገሪቱን ቅርጽ እንዲወስኑ እድል ሰጥቷቸዋል ፣ ይህም ዴሞክራሲ ፣ መሰረታዊ መብት እና ነጻነታችን ላይ አደጋ የደቀነ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
የ82 አመቱ ተሰናባች ፕሬዝዳንት በቴክኖሎጂ እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰሚነት ያላቸው ጥቂት ግለሰቦች ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉም አሳስበዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በተለያዩ ዘርፍ የጠቀሷቸው በአሜሪካ ዴሞክራሲ እና ሌሎችም መሰረታዊ መርሆች ላይ ጫና ያሳድራሉ ያሏቸውን ሰዎች በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡
ነገር ግን በጥቂት የናጠጡ ሀብታሞች እጅ ስላለው እጅግ አደገኛ ሀይል እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሲናገሩ ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያለውን ኢለን መስክ ለማለት ፈልገው ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በመሰናበቻ ንግግራቸው የአየር ንብረት ለውጥ እና የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት የመጪው ጊዜ ጠንካራ ተግዳሮቶች ሆነው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት፡፡
በቅርቡ ገለልተኛ የእውነታ አጣሪዎችን እንደሚያስወግድ ያስታወቀውን ሜታ ኩባንያን የወቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤
"ማህበራዊ ሚዲያው እውነትን ማጣራት ትቷል፣ እውነትም ለስልጣን እና ለጥቅም ሲባል በሚወራ ውሸት ተሸፍኗል" ሲሉ የመረጃ ነጻነት እና ሀቀኝነትን ማስቀጠል የማህበራዊ ሚዲያን ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ለመቆጣጠር መሳሪያ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።::
ባይደን በአንድ የስልጣን ዘመን ያሳኳቸውን ስኬቶች ሲዘረዝሩ በክብረወሰን የተመዘገበ የስራ እድል መፍጠራቸውን፣ የመሠረተ ልማት እደሳትና ግንባታ ወጪን፣ የጤና አጠባበቅን፣ ሀገሪቱን በወረርሽኝ ወቅት በተሳካ ሁኔታ መምራታቸውን እና ሌሎችንም ነጥቦች አንስተዋል፡፡
አክለውም "ያሳካናቸውን ስኬቶች ለመገንዘብ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ነገር ግን ዘሩን ተክለነዋል በሚቀጥሉት አመታት ፍሬ አፍርቶ ትመለከታላችሁ” ነው ያሉት ፡፡
በመጨረሻም አሜሪካውያን ሀገራቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ አደራ በማለት የስንብት ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡