የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ዘመን ምን ሊመስል ይችላል?
በማይናማር የታገቱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም ተብሏል
ኢትዮጵያ በቅርቡ አምባሳደሯን ወደ ሞቃዲሾ እንደምትልቅ ገልጻለች
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ዘመን ምን ሊመስል ይችላል?
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስላሉ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ ከተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ስለ ሚኖራት ግንኙነት እና ሌሎችም ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው።
አምባሳደር ነቢያት በህገወጥ ደላሎች እና ዓለም አቀፍ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተታለው ወደ ማይናማር የሄዱ እና የታገቱ ኢትዮጵያዊያንን ለማስለቀቅ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ልክ እንደ ኢትዮጵያዊያኑ ሁሉ በማይናማር የ19 ሀገራት ዜጎች ታግተው ይገኛሉ ያሉት አምባሳደር ነቢያት ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
በማያንማር ታግተው ካሉ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ የ380 ዜጎች ፓስፖርት ኮፒ በጃፓን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ተልኮ ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ ነውም ተብሏል።
በማይናማር ታግተው ያሉ ኢትዮጵያዊያን ብዛት ይታወቃል? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም "ጉዞው ህገወጥ በመሆኑ ምን ያህል ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በማይናማር እንደታገቱ አይታወቅም፣ ወደ ቶኪዮ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የተላከው ፓስፖርት ቁጥር እና ፎቶም ከቤተሰቦቻቸው የተገኘ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በእገታ ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ለማስለቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ከባድ ያደረገው አጋቾቹ ያሉበት ቦታ በማይናማር እና ታይላንድ ድንበር አካባቢ መሆን እና ቦታዎቹ ከማይናማር መንግሥት ቁጥጥር ውጭ መሆናቸው እንደሆነም አምባሳደር ነቢያት ተናግረዋል።
ሌላኛው ለቃል አቀባዩ ከቀረበላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ከተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ምን አይነት ግንኙነት ሊኖራት ይችላል? የሚለው ነበር።
ቃል አቀባዩ በምላሻቸውም "ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ለ120 ዓመት የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው፣ በዶናልድ ትራምፕ ከሚመሰረተው አዲስ መንግሥት ጋርም ብሔራዊ ጥቅማችንን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ይኖረናል" ሲሉ አጭሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ አምባሳደሯን ወደ ሞቃዲሾ እንደምትልክም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት መሻከሩ ይታወሳል።
በቱርክ መዲና አንካራ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች ባደረጉት ስምምነት አለመግባባታቸውን ለመፍታት እና ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸውን ተከትሎ በሞቃዲሾ ያለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ያሉ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ቀድሞ ስራቸው ይገባሉም ተብሏል።