በዓለ ሲመቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ 25 ሺህ የጸጥታ ሃይሎች ይሰማራሉ ተብሏል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በዓለ ሲመት በየአራት አመቱ ጥር 20 ይካሄዳል። ጥር 20 እሁድ ከዋለ ደግሞ ጥር 21 ላይ ይደረጋል።
ጆ ባይደን በ2021 በዓለ ሲመታቸው ሲካሄድ 46 ፕሬዝዳንቶች በተለያየ ጊዜ ለ73 ጊዜ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
22 ፕሬዝዳንቶች ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ተመርጠው በድጋሜ ቃለመሃላ የፈጸሙ ሲሆን፥ በህዳር ወር በተካሄደው ምርጫ ዴሞክራቷን ካማላ ሃሪስ በሰፊ ልዩነት ያሸነፉት ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ የፊታችን ሰኞ ለሁለተኛ ጊዜ ቃለ መሃላ ፈጽመው ወደ ነጩ ቤተመንግስት ይገባሉ።
ከቃለመሃላው በፊት ግን የተለያዩ መርሃ ግብሮች ይካሄዳሉ።
ቅዳሜ ጥር 18 2025 በቨርጂኒያ በሚገኘው የትራምፕ የጎልፍ ክለብ ከሚካሄደው ደማቅ የርችት ስነስርአት ጀምሮ በአርሊንግተን እና ዋሽንግተን ዲሲ የተለያዩ ዝግጅቶች ይደረጋሉ።
ትራምፕ ሰኞ በካፒቶል አዳራሽ ቃለመሃላ ፈጽመው በይፋ ወደ ዋይትሃውስ ገብተው ስራ ቢጀምሩም የበዓለ ሲመት ዝግጅቱ የሚጠናቀቀው ማክሰኞ የተለያዩ የእምነት ተከታዮች በዋሽንግተን ብሄራዊ ካቴድራል ጸሎት ካደረጉ በኋላ ነው።
የ47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት የሽብር ጥቃት ስጋት እንዳንዣበበበት የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት አስታውቀዋል።
በዓለ ሲመቱ በሰላም እንዲጠናቀቅም 25 ሺህ የሚጠጉ የጸጥታ ሃይሎች እንደሚሰማሩ ተገልጿል።