የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት በዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል አስጠነቀቁ
የደህንነት ተቋማቱ በምርጫ ውጤቱ የተበሳጩ አካላት ውጤቱን ባለመቀበል የመጨረሻ የጥቃት ሙከራቸውን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው ያሳሰቡት
በስነስርአቱ ላይ ፖሊስ እና ወታደሮችን ጨምሮ 25 የጸጥታ አካላትእንደሚሰማሩ ይጠበቃል
ከሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ያመለጡት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት አስጠንቅቀዋል፡፡
በአለ ሲመቱ ለአመጽ እና ብጥብጥ የተጋለጠ መሆኑን ያስጠነቀቁት የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ተቋማት በጥበቃ እና ደህንነት ስራዎች ላይ ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡
የስለላ ኤጄንሲዎች የህግ አስከባሪ ተቋማት በጋራ ባደረጉት ግምገማ ወንጀለኞች በተለይም ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ ቅሬታ የገባቸው ወገኖች፤ በምርጫ ውጤቱ ላይ በአመጽ ተጽእኖ የመፍጠር በዓለ ሲመቱን የመጨረሻ እድል አድርገው ሊመለከቱት እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡
የውጭ አሸባሪዎች፣ የሀገር ውስጥ “ፅንፈኞች” እና ግለሰቦች የድሮን ጥቃቶችን፣ ተሸከርካሪዎችን በሰዎች ላይ በመንዳት እንዲሁም በሌሎች ዘዴዎች ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ተቋማቱ ስጋት አድሮባቸዋል፡፡
ስጋቱ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ሁከትና ብጥብጥ የተላበሰ የፖለቲካ ምህዳር የሚያንፀባርቅ ነው ሲል ፖሊቲኮ መጽሔት ዘግቧል።
ይህን ተከትሎም ከ6 ቀናት በኋላ የሚከናወነውን ስነስርአት ደህንነት ለማስጠበቅ ተጨማሪ የተጠናከረ ጥበቃ ዝግጅት እና የስጋት ትንተናዎች በስፋት መከናወን እንደሚገባቸው ተቋማቱ አሳስበዋል፡፡
በጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ ግድያ ምክንያት ኢራን በፕሬዝዳንቱ ላይ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች በሚል በስጋትነት ከተለዩ የውጭ አካላት መካከል ተመድባለች፡፡
የዋሽንግተን ፖሊስ አዛዣ ፓሜላ ስሚዝ ሰኞ እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ፖሊሶች ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚገቡና 4 ሺህ የሚጠጉ የፖሊስ መኮንነኖች እንደሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡
ይህም ቃለ መሀላው የሚከናወንበት የካፒቶል ሂል ፖሊሶችን ለመደገፍ ከተሰማሩ 1000 ፖሊሶች በተጨማሪ የሚመደቡ ናቸው፡፡
በተመራጩ ፕሬዝዳንት ላይ በ2024 የምርጫ ዘመቻ ወቅት ሁለት የግድያ ሙከራዎች መደረጋቸወን ተከትሎ እና በዚህ አመት በኒው ኦርሊንስ እና በላስቬጋስ ተከታታይ የሽብር ጥቃቶች በመፈጸማቸው የጸጥታ እና ደህንንት ባለስልጣናት ሁኔታዎችን በንቃት እየመረመሩ ይገኛሉ፡፡
በበዓለ ሲመቱ ላይ በአጠቃላይ 25 ሺህ የሚጠጉ የህግ አስከባሪ አካላት እና ወታደሮች እንደሚሰማሩ ቢነገርም በስነስርአቱ ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎች ወደ ብጥብጥ ሊቀየሩ እንደሚችሉ የደህንነት ተቋማቱን አሳስበዋል፡፡