ባይደን በእስራኤል ላይ “በቅርቡ” ጥቃት ታደርሳለች ያሏትን ኢራን አስጠነቀቁ
ዋሽንግተን አጋሯን ከጥቃት ለመጠበቅ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተጨማሪ ሀይል የላከች ሲሆን የጦር መርከቦቿ እንዲንቀሳቀሱ አዛለች
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ 40 የሚጠጉ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል መተኮሱ ተገልጿል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቱ ኢራን “በቅርቡ” በእስራኤል ላይ ጥቃት ለማድረስ ማቀዷን ገልጸው፥ ቴህራን ውጤታማ ከማይሆን ጥቃቷ እንድትቆጠብ ጠይቀዋል።
“አሜሪካ የእስራኤልን ደህንነት ለማስጠበቅ የትኛውንም ድጋፍ ታደርጋለች” ያሉት ባይደን፥ ለቴህራን “እንዳትሞክሪው” የሚል መልዕክት ሰደዋል።
ኢራን በሶሪያ መዲና ደማስቆ በሚገኝ ቆንስላዋ ለተፈጸመው ጥቃት ቴል አቪቭን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን፥ የሀገሪቱ ሀይማኖታዊ መሪ አሊ ካሚኒ የአጻፋ እርምጃ እንደሚወሰድ መዛታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ዝርዝር መረጃ መስጠት ባይፈልጉም ቴህራን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥቃት እንደምታደርስ የሚያመላክት መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋሽንግተን በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የጦር መርከቦቿን እስራኤል ከኢራን ሊቃጣባት የሚችለውን ጥቃት መመከት በሚያስችል ስፍራ እንዲሆኑ አዛለች፤ ወደ ቀጠናው ተጨማሪ ሃይል መላኳም ተሰምቷል።
ኢራን የፍልስጤሙን ሃማስ፤ የየመኑን ሃውቲ፤ የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን እንደምትደግፍ ይነገራል።
ሄዝቦላህ በትናንትናው እለት ወደ እስራኤል 40 የሚጠጉ ሚሳኤሎች መተኮሱ የተነገረ ሲሆን፥ እስካሁን የደረሰው ጉዳት ግን አልተገለጸም።
የሄዝቦላህ ጥቃት ኢራን በእስራኤል ላይ እፈጽመዋለሁ ካለችው ጥቃት ጋር እንደማይገናኝ ሲቢኤስ ቴሌቪዥን የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ተንታኞች አለም አይኑን እስራኤል ላይ ባደረገበትና ጣቱን ኢራን ላይ ለመቀሰር በሚጠባበቅበት በአሁኑ ወቅት ቴህራን ጥቃቱን ታደርሳለች ተብሎ እንደማይጠበቅ ገልጸዋል።
በደማስቆ ጀነራሎቿ የተገደሉባት ኢራን ጠንካራ የአጻፋ እርምጃ እንድትወስድ አያቶላህ አሊ ሃሚኒን ጨምሮ በርካታ ኢራናውያን ፍላጎት ቢኖራቸውም ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ የሚያዙት እርምጃ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የሚያስገባ እንዲሆን አይፈለግም ተብሏል።
የጋዛው ጦርነት የመካከለኛው ምስራቅ ባላንጣነታቸውን ይበልጥ ያባባሰባቸው ኢራን እና እስራኤል ውጥረታቸውን እንዲያረግቡ ሀገራት እየጠየቁ ነው።
አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ አውስትራሊያ እና ፖላንድን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው ወደ እስራኤል እንዳያመሩና በማሳሰብ ላይ ናቸው።