እስራኤል ሶሪያ ውስጥ በኢራን ቆንስላ ጽ/ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት 2 ጀነራሎች መገደላቸውን ኢራን ገለጸች
ይህ ጥቃት እስራኤል በኢራን ይደገፋል በሚባለው የሄዝቦላ ታጣቂ ላይ እያደረሰችው ያለው ጥቃት መጨመሩን ያሳያል ተብሏል
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ናስር ከናኒ ሀገራት ይህን ጥቃት እንዲያወግዙት ጠይቀዋል
እስራኤል ሶሪያ ውስጥ በኢራን ቆንስላ ጽ/ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት 2 ጀነራሎች መገደላቸውን ኢራን ገለጸች።
እስራኤል በትናንትናው እለት ሶሪያ ውስጥ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ጽ/ቤት ህንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ጀነራሎች እና አምስት ሰራተኞች መገደላቸውን ኢራን አስታውቃለች።
ይህ ጥቃት እስራኤል በኢራን ይደገፋል በሚባለው እና በሊባኖስ እና እስራኤል ድንበር በሚንቀሳቀሰው የሄዝቦላ ታጣቂ ላይ እያደረሰችው ያለው ጥቃት መጨመሩን ያሳያል ተብሏል።
ሄዝቦላ ከእስራል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ያለውን አጋርነት ለማሳየት ከእስራኤል ጋር ግጭት ውስጥ የገባው ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤል እና ሀማሰ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር።
ጦርነቱ ከተጀመረ ስድስት ወር ያስቆጠረ ሲሆን በእስራኤል እና ሄዝቦላ መካከል ያለው ውጥረት እያየለ መጥቷል።
ኢራን ጋዛን የሚያስተዳድረውን እና ባለፈው ጥቅምት ሰባት በእሰራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት የከፈተውን ሀማሰን ትደግፋለች የሚል ክስ በእስራኤል በኩል ይቀርባታል።
የኢራን ኢላማዎችን ማጥቃቷን አልፎ አልፎ የምታምነው እስራኤል በዚህ ጥቃት ጉዳይ አስተያየት እንደሌላት ገልጻለች። በቆንስላ ጽ/ቤቱ ላይ ከደረሰው ጥቃት ቀደም ብሎ የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ በደቡብ እስራኤል በሚገኘው የባህር ኃይል ላይ ለደረሰው የድሮን ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርጓል።
ከሄዝብላህ ጋር በየቀኑ የተኩስ ልውውጥ እያደረገች ያለችው እስራኤል ትግስቷ እያለቀ መሆኑን እና ወደ አጠቃላይ ጦርነት ልትገባ እንደምትችል አስጠንቅቃለች።
በየመን የሚገኙት በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች ትናንትን ጨምሮ በረጅም ርቀት ሚሳይል እስራኤልን በማጥቃት ላይ ናቸው።
በሶሪያ በተካሄደው የአየር ጥቃት የኢሊት ኩድስ ፎርስን ሲመሩ የነበሩት ጀነራል መሀመድ ሬዛ ዛኸዲ መገደላቸውን የኢራን ሪቮሉሽነሪ ጋርድ አስታውቋል። የዛኸዲ ምክትል ጀነራል ሀዲ ሀጂራሂሚ እና ሌሎች አምስት ሰራተኞች በጥቃት ተገድለዋል።
በዚሁ ጥቃት የሄዝቦላ አባል የሆነው ሁሴን የሱፍ መገደሉንም ኤፒ ዘግቧል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ናስር ከናኒ ሀገራት ይህን ጥቃት እንዲያወግዙት ጠይቀዋል።
እስራኤል ባለፉት አመታት የመሳሪያ ዝውውር እና ከሄዝቦላ ጋር የሚደረግ ትብብርን ለማስተጓጎል በማሰብ በሶሪያ ውስጥ የኢራን ኢላማዎችን ስታጠቃ ቆይታለች።