ኢራን ዛሬ ወይም ነገ እስራኤልን ልታጠቃ እንደምትችል አሜሪካ ገለጸች
በቴልአቪቭ እና እየሩሳሌም የሚኖሩ አሜሪካዊያን ራሳቸውን ከእንቅስቃሴ እንዲያቅቡ አስጠንቅቋል
እስራኤል በበኩሏ ከባድ ጊዜ ላይ መሆኗን ገልጻ ለሚደርስባት ማንኛውም ጥቃት የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች
ኢራን ዛሬ ወይም ነገ እስራኤልን ልታጠቃ እንደምትችል አሜሪካ ገለጸች።
እስራኤል ባሳለፍነው ሳምንት በሶሪያ መዲና ደማስቆ በሚገኝ የኢራን ኢምባሲ ላይ ባደረሰችው ጥቃት ሁለት ወታደራዊ አዛዦችን ጨምሮ ዘጠኝ ኢራናዊ ተገድለዋል ተብሏል።
ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቷን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ነግሷል።
ዎል ስትሬት ጆርናል የአሜሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለርን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ኢራን ዛሬ ወይም ነገ በእስራኤል ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች።
ኢራን ከ12 ቀናት በፊት በደማስቆ በሚገኘው ኢምባሲዋ ላይ ለደረሰባት ጥቃት የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀት እንደሆነም ተገልጿል።
በእስራኤል የአሜሪካ ኢምባሲ ባወጣው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ኢራን በደቡባዊ እና ሰሜናዊ የእስራኤል አካባቢዎች ላይ ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል አስታውቋል።
በመሆኑም በቴልአቪቭ እና እየሩሳሌም ከተሞች አሜሪካዊያን ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ ሲልም ኢምባሲው አስጠንቅቋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን አሜሪካ ከእስራኤል ጎን እንደምትቆም የገለጹ ሲሆን የጦር ጀነራሏን ለተጨማሪ ድጋፍ ወሰ ቴልአቪቭ ልካለች።
እስራኤል በበኩሏ ኢራን ከራሷ ግዛት ላይ የተነሳ ጥቃት ካደረሰች የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
ጠቅላይ ሚንስትር ቤን ያሚን ኔትያናሁ የእስራኤል አየር ሀይል ዋና ማዘዣ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር "ከባድ ጊዜ እያሳለፍን እንገኛለን" ብለዋል።
እስራኤል የሚደርስባትን ማንኛውንም ጥቃት መመከት እንደምትችል የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ በሐማስ የታገቱ ዜጎችን ለማስለቀቅ የጋዛ ዘመቻቸውን እንደሚቀጥሉበትም ተናግረዋል።
ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃት በቀጥታ አልያም በሌላ ወገን ጥቃት ታደርሳለች የሚለው ስጋት እየጨመረ መጥቷል።
በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እንዳይጓዙ ያስጠነቀቁ ሲሆን አየር መንገዶችም በረራቸውን እየሰረዙ እና እያራዘሙ ናቸው።