እስራኤል በሶሪያ ኢራናዊ ጀነራልን መግደሏ ቴህራንን ክፉኛ አስቆጥቷል
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ “እስራኤል ፍርሃት ለወለደው እርምጃዋ ዋጋዋን ታገኛለች” ሲሉ ዝተዋል
የጀነራሉ ግድያ በጋዛው ጦርነት ይበልጥ የተባባሰውን የእስራኤልና ኢራን ፍጥጫ እንዳያንረው ተሰግቷል
እስራኤል በሶሪያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዥን መግደሏ ተገልጿል።
የኢራን ብሄራዊ ቴሌቪዥን መደበኛ ዜናዎችን አቋርጦ ሳይድ ራዚ ሙሳቪ የተባሉት ግለሰብ መገደላቸውን ዘግቧል።
ሙሳቪ በኢራንና ሶሪያ መካከል ወታደራዊ ጥምረት በመመስረት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ነብራቸው ተብሏል።
- በኢራቅ እና በሶሪያ ባለው የአሜሪካ ጦር ላይ ለደሰረው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደው ማነው?
- ኢራን ከቀይ ባህር ውጪ ተጨማሪ የዓለም ባህር ትራንስፖርት መስመር አቋርጣለሁ አለች
ግለሰቡ አሜሪካ በ2020 በኢራቅ ከገደለቻቸው ቃሲም ሱሌማኒ ጋር ከነበሩ ከፍተኛ አማካሪዎች አንዱ እንደነበሩም ነው የተገለጸው።
በሶሪያ ጉዳይ የቴህራን ቁልፍ ሰው የነበሩት ሙሳቪ ከስራ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በእስራኤል ሚሳኤል መመታታቸውን በሶሪያ የኢራን አምባሳደር ሁሴን አክባሪ ተናግረዋል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ የሙሳቪ ግድያ የእስራኤልን ደካማነት ያሳያል ብለዋል።
“የእስራኤል እርምጃ በቀጠናው አቅም ማጣቷንና ፍርሃቷን ያሳያል፤ በርግጠኝነት ለዚህ እርምጃዋ ዋጋዋን ታገኛለች” ሲሉም ዝተዋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብም ብርጋዴር ጀነራልነት ድረስ የዘለቀ ማዕረግና ጉልህ አበርክቶ የነበራቸው ሙሳኒ መገደላቸው እንዳበሳጨውና ለቴል አቪቭ አጻፋውን እንደሚመልስ ገልጿል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ በበኩላቸው “ኢራን ለዚህ ጥቃት ተገቢውን ምላሽ በፈለገችው ስፍራ እና ጊዜ የመውሰድ መብት አላት” ብለዋል።
የፍልስጤሙ ኢስላሚክ ጂሃድ ሙሳቪ በቀጠናው ለሚደረጉ የነጻነት ትግሎች የነበራቸውን ድጋፍ በማንሳት ግድያውን “አስነዋሪ ድርጊት” ነው በሚል ተቃውሞታል።
የእስራኤል ጦር ግን ስለወታደራዊ መኮንኑ ግድያ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠችም።
የጦሩ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኔል ሃጋሪም ከጋዜጠኞች ስለግድያው ተጠይቀው፥ “የእስራኤል ጦር የሀገሪቱን ደህንነት ማስጠበቅ ይኖርበታል፤ ለውጭ ሪፖርቶች አስተያየት አልሰጥም” በሚል ማስተባበልም ሆነ ማረጋገጥ አለመፈለጋቸውን አሳይተዋል።
እስራኤል በዚህ ወር መጀመሪያ የሶሪያ ጦርን የሚያማክሩ ሁለት የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባላትን መግደሏን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።