ጆ ባይደን አሜሪካ የኔቶን ግዛት “እያንዳንዱን ኢንች” እንደምትከላከል ፑቲንን አስጠነቀቁ
ሩሲያ፤ የዩክሬን ክልሎች “ለዘላለሙ” የሩሲያ አካል መሆናቸው በይፋ ማወጇ ውጥረቱን እንዳያባብሰው ተሰግቷል
ፕሬዝዳንት ባይደን “አሜሪካም ሆነ አጋሮቿ ኃላፊነት በጎደላቸው የፑቲን ዛቻዎች የሚደናገጡ አይደሉም” ብለዋል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፤ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በኔቶ ግዛት ላይ ምንም አይነት ስጋት እንዳይፈጥሩ በጥብቅ አስጠንቅቀዋል።
"አሜሪካ እያንዳንዱን ኢንች የኔቶ ግዛት ለመከላከል ከኔቶ አጋሮቻችን ጋር ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅታለች፤ እያንዳንዱ ኢንች ፣ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“ሚስተር ፑቲን በተሳሳተ መንገድ እትረዳኝ ፤ እያንዳንዱ ኢንች ነው ያልኩት” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ወደ ሩሲያ የተቀላቀሉትን አዳዲሶቹን የዩክሬን ግዛቶች ለመጠበቅ ኒውክሊየር ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል የዛቱት ፑቲን ግዛቶቹ “ለዘላለሙ” የሩሲያ አካል መሆናቸው በይፋ ማወጃቸው ውጥረቱን እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡
ፑቲን ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር አገራቸው “በርካታ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን መታጠቋን” ገልጸው፣ አስፈላጊ ሲሆን ያለንን አማራጭ ሁሉ እንጠቀማለን ብለዋል። ይህንን የምለው ለማስፈራራት አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።
በአዳዲሶቹ ግዛቶች ላይ የሚቃጣ ማንኛው አይነት ጥቃት በሩሲያ ላይ እንደተቃጣ ይቆጣራልም ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡
ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰጡት ምላሽ “ሀገራቸውም ሆነ አጋሮቿ በቭላድሚር ኃላፊነት በጎደላቸው የፑቲን ዛቻዎች የሚደናገጡ አይደሉም” ሲሉ ለክሬምሊን ባለስልጣናት ጠጠር ያለ መልዕክት አስተላለፍዋል።
የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ የግዛቶቹን መጠቅለል “ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የታየ እጅግ አሳሳቢው ክስተት” ነው ብለዋል።
ግዛቶቿ ወደ ሩሲያ የተጣቀለሉባት ዩክሬን በአስቸኳይ የኔቶ አባል እንድትሆን ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ የሩሲያን እርምጃ የተቃወሙት የኔቶ አባላት ምን እንደሚወስኑ በቀጣይ ሳምንታት ይሚታወቅ ይሆናል።
የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያ የተያዙባቸውን ግዛቶቻቸው ለማስመለስ ወታደራዊ ዘመቻዎችን እያካሄዱ ሲሆን፣ የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አርብ ዕለት እንዳሳወቀው የዩክሬን ኃይሎች አንዳንድ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪም ጦራቸው ሁሉንም ግዛቶቻቸውን ከሩሲያ ወረራ እስከሚያስለቅቅ ድረስ ፍልሚያቸውን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከምዕራቡ ዓለም ጋር የገባችበት ከፍተኛ ውጥረት ብዙ መልክ እያስተናገደ እንደቀጠለ ነው፡፡