አሜሪካ ሱዳን ለሩሲያ የጦር ሰፈር ብትፈቅድ “መዘዙ ከባድ ይሆናል” ስትል አስጠነቀቀች
እንደፈረንጆቹ በ2017 በአልበሽር እና ፑቲን መካካል “የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ስምምነት” መፈረሙ የሚታወስ ነው
አምባሳደር ጆን ጎድፍሬ ሩሲያ በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ የጦር ሰፈር ልትከፍት እንደሆነ የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው ብለዋል
በሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር ጆን ጎድፍሬ ፤ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገረ ሱዳን በቀይ ባህር ዳርቻ ለሩሲያ የጦር ሰፈር ብትፈቅድ “መዘዙ ከባድ ይሆናል” ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡
አምባሳደር ጆን ጎድፍረይ ከታይያር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ሩሲያ በቀይ ባህር ላይ የጦር ሰፈር ለመመስረት እንደፈረንጆቹ በ2017 ከስልጣን ከተወገዱት ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እየጣረች ነው የሚሉ አንዳንድ ሪፖርቶች አሉ" ብለዋል።
“ሁሉም ሀገሮች ከየትኞቹ ሀገሮች ጋር አጋር እንደሚሆኑ የመወሰን ሉዓላዊ መብት ቢኖራቸውም አንዳንድ ምርጫዎች መዘዞች ሊያስከትሉ ይችላሉ” ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
አምባሰደሩ ይህ የሚሆን ከሆነ ሱዳንን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚነጠል እና የሀገሪቱን ጥቅም የሚጎዳ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
አሜሪካ ጥሩ አጋር ልትሆን የምትችል ቢሆንም ፤ ይህ የሚሆነው አዲስ በሲቪል የሚመራ መንግስት እና የሽግግር ማእቀፍ በመፍጠር ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና እንድተመለስ ማድረግ ሲቻል መሆኑ አምባሳደሩ መናገራቸው የቱርኩ አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2019 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተወገዱት ፕሬዝዳንት በሽር በህዳር 2017 ሞስኮን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ ስልጠና፣ በተሞክሮ መጋራት እና የጦር መርከቦች ወደ ሁለቱ ሀገራት ወደቦች እንዲገቡ የሚያስችሉ የትብብር ስምምነቶችን መፈራረማቸው ይታወሳል።
እንደ ሩሲያ ቱዴይ ዘገባ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ በሱዳን የኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ማስተናገድ የሚችል የሩሲያ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ለማቋቋም የሚያስችል ውሳኔ በህዳር 16 ቀን 2020 አጸድቀው ነበር፡፡
ያም ሆኖ የሱዳን ጦር ሃይል አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሀመድ ኡስማን አል ሁሴን ከሶስት ቀናት በኋላ በሰጡት መግለጫ “በቀይ ባህር የባህር ሃይል ጦር ሰፈር ለማቋቋም ከሩሲያ ጋር ሙሉ ስምምነት ባይኖርም ወታደራዊ ትብብራችን እንዲራዘም ተደርጓል" ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
እንደፈረንጆቹ ታህሳስ 9 ቀን 2020 የሩሲያ ሚዲያ ይዞት የወጣው ዘገባ በሩሲያ እና በሱዳን መካከል በቀይ ባህር ላይ ለሩሲያ የባህር ኃይል አቅርቦት እና ጥገና ጣቢያ ለማቋቋም የተደረሰውን ስምምነት “የአከባቢውን ሰላም እና ደህንነት ለመደገፍ” ያለመ ነው ማለቱም የሚታወስ ነው፡፡