“አሜሪካ ህወሓትን ትደግፋለች”ተብለው የተጠየቁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ምን አሉ ?
ቃል አቀባዩ፤ አሜሪካ ግጭቱን ለማስቆም የአፍሪካ ህብረትን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ትደግፋለች ብለዋል
ኔድ ፕራይስ፤ እኛ ምንደግፈው የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ነው ብለዋል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በትናትናው እለት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከጋዜጠኖች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምለሽ ሰጥተዋል፡፡
ለቃል አቀባዩ ከቀረቡ ጥያቄዎች ፤ “እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት ብዙ ጊዜ ተናግረሃል። የኢትዮጵያ ጦር ወደ ትግራይ ክልል ሲገባ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሌሎች ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል እንዲያወጣ ደጋግሞ ጠይቋል። ነገር ግን የህወሓት ታጣቂዎች ወደ አማራ እና አፋር ክልል ሲገቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት - ህወሓትን ከአማራ እና አፋር ክልል እንዲያወጣ ከመጠየቅ ይልቅ ሁለቱም ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ሲጠይቅ ይሰተዋላል። አሁንም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ህወሓትን ትደግፋለች ብሎ ያምናል፤ አሜሪካ ለምድነው ህወሓትን የምትደግፈው ብሎ ይጠይቃል። አሜሪካ ህወሓትን ትደግፋለች ለሚሉት ኢትዮጵያውያን ምን ምላሽ አለህ? የሚል ነበር፡፡
ቃል አቀባዩ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ ፤ “እኛ ምንደግፈው ሰላም ነው ፤ድጋፋችን ለኢትዮጵያ ህዝብ መረጋጋት እና ደህንነት ነው፤ ሁልጊዜም ቢሆን መልእክታችን ግልጽ ነው በማለት አሜሪካ ህወሓትን የምትደግፍበት የተለየ ምክንያት እንደሌላት አስረድተዋል፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ወታደራዊ ጥቃትን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሰላማዊ ድርድር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበናል፤ ከአፍሪካ ህብረት እና ከአህጉሪቱ አጋሮች ጋር በመሆንም በዲፕሎማሲ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ተቀራርበን በመስራት ላይ ነን” ብለዋል፡፡
ከኤርትራ ጋር በተያያዘ የኤርትራ ጦር ባስቸኳይ ወደ ድንበራቸው መውጣት እንዳለበት እንዲሁም የኤርትራ ባለስልጣናት ቀውሱን ከማባባስ እንዲቆጠቡ አሜሪካ በግልጽ ስትናገር መቆየቷም አስታውሰዋል ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ፡፡
“በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ያስከተለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በጣም አሳስቦናል” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ይዞት የሚመጣው እድል መጠቀሙ እጅግ የላቀ ጠቀሜታ አለው ብለን እናምናለን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኔድ ፕራይስ፤ ግጭቱን ለማስቆም አፍሪካ ህብረት በሚያደረጋቸው የዲፕሎማሲ ጥረቶች ሁሉ አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በድርድር እንዲቋጭ አሜሪካንን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ለወራት ሲያደርጉት የቆየውን የሽምግልና ጥረት ይህ ነው የሚባል ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሄ እንዳላመጣ በርካቶች የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡
ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ቢሆንም ግን፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእከተኛ ማይክ ሐመር አሁንም የድርድር ተስፋ መኖሩ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ሁለቱም ወገኖች የጦርነት አማራጭን ትተው በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ የሚያስችል “ደፋር ውሳኔ እንደሚወስኑ ተስፋ አለን”ም ነበር ያሉት ልዩ መልእክተኛው።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለወራት ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም ድጋሚ መቀስቀሱ ይታወሳል።
ጦርነቱን እንደ አዲስ በመጀመር መንግስት እና ህወሓት እርስ በእርስ ሲካሰሱ ይስተዋላል፡፡
ያም ሆኖ ሁለቱም አካላት የተደጀመረውን ሰላም ንግግር ጥረት እንዲቀጥል ዝግጁ መሆናቸው ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በድጋሚ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛው ቦታ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ከህወሓት ጋር እንደሚደራደር ዝግጂ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
አፍሪካ ህብረት “ሰላም ሊያመጣ አይችልም” አስከማለት ደርሶ የነበረው ህወሓትም ቢሆን ፤በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄደው የሰላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡