የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ደቡብ ኮሪያ ገቡ
የምክትል ፕሬዝዳንቷ ጉብኝት አሜሪካ የደቡብ ኮሪያን ደህንነት ለማስጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው ተብሏል
ካማላ ሃሪስ ፤ ሴኡል የገቡት ሰሜን ኮሪያ ሚሳዔሎች ካስወነጨፈች ከሰዓታት በኋላ ነው
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ደቡብ ኮሪያ ገቡ።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ሴኡል ገቡት ሰሜን ኮሪያ ጃፓን እና ሁለቱም ኮሪያዎች ወደሚያዋስነው የምስራቅ ባህር ክልል ሁለት የባላስቲክ ሚሳዔል ካስወነጨፈች ከሰአታት በኋላ ነው።
ሃሪስ ሴኡል ሲደርሱ ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ-ዮል ጋር የተገናኙ ሲሆን በቀጠናው የሰላምና ደህንነት ጉዳይ መምከራቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ካማላ ሃሪስ እና ዩን ሱክ-ዮል የፒዮንግያንግን "ተንኳሽ የኒውክሌር ትርክት እና የባላስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፍ ድርጊት" ማውጋዛቸውንና የኮሪያን ልሳነ ምድርን ሙሉ በሙሉ ከኒውክሌር ነጻ የማድረግ የጋራ ግባቸውን ለማሳካት በጋራ የመስራቱ ጉዳይ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ከስምምነት መድረሳቸው ዋይት ሃውስ አስታውቋል፡፡
ጉብኝቱ አሜሪካ የደቡብ ኮሪያን ደህንነት ለማስጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነትን የሚያሳይ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡
ፒዮንጊያንግ በትናንትናው እለት ሱናን ከሚባለው አካባቢ ሚሳዔሎች ማስንጨፏ የደቡብ ኮሪያና አሜሪካ የጋራ ወታደራዊ አዛዦች መግለጻቸው አይዘነጋም።
ሚሳዔሎቹ ወደ 360 ኪሎ ሜትር በመብረር 30 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ የመምዘግዘግ አቅም እንዳላቸው የገለጹት አዛዦቹ፤ የፒዮንጊያንግ ትንኮሳ የሴኡል-ዋሽንግተን ጥምረት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
"የሰሜን ኮሪያ ትንኮሳ የደቡብ ኮሪያ-አሜሪካን የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት አቅም የበለጠ ያጎለብታል እንዲሁም እና ሰሜን ኮሪያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የመገለሏ ጉዳይ የበለጠ የሚያጠናክር ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የፒዮንጊያንግ ድርጊት ከሴኡልና ዋሽንግተን በተጨማሪ የቲክዮ ባለስልጣናትም አውግዘውታል፡፡
የጃፓን መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታው ቶሺሮ ኢኖ ፤ የፒዮንጊያንግ ድረጊት "ተቀባይነት የለውም" በማለት ሰሜን ኮሪያ በትናንትናው እለት የፈጸመችውን የሚሳዔል ማስወንጨፍ ድርጊት ኮንነዋል፡፡
መከላካያ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ የባለስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፍን ጨምሮ የምትወስዳቸው ተከታታይ እርምጃዎች፣ ለጃፓን፣ ለቀጣናው እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላምና ደህንነት ስጋት ፈጥረዋል" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የሚሳዔሎቹ ማስወንጨፍ ሙከራን በተመለከተ በሰሜን ኮሪያ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም ቀደም ሲል የሀገሪቱ መሪ ኩም ጆንግ ኡን “ፒዮንጊያንግ የኒውክሌር እና ሚሳዔሎች ባለቤት የመትሆነው ራሷን ካምንኛውም ጥቃት ለመከላከል ነው” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡