ብሊንከን በኢትዮጵያ “እየተባባሰ ስለመጣው የሰብአዊ ቀውስ” ያላቸውን ስጋት ለጠ/ ሚ ዐቢይ በስልክ ገለጹ
ብሊንከን ከጠ/ሚ ዐቢይ ጋር በስልክ ተወያይተዋል
አሜሪካ በትግራይ ያለው የረሃብ ተጋላጭነትና በሌሎች አካባቢዎች ያለው አለመረጋጋት እንደሚያሳስባት ገለጸች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና በኢትዮጵያ “እየተባባሰ ስለመጣው የሰብአዊና የሰብአዊ መብት ቀውስ”ያላቸውን ስጋት በአጽንኦት መናገራቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ውይይቱን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ የለም፡
ብሊንከን በትግራይ ያለው የረሃብ ተጋላጭነት እንሁም በሌሎች አካባቢዊች ያለው አለመረጋጋት አሜሪካን እንደሚያሳስባት ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ኤርትራ በተስማሙት መሰረት የኤርትራ ጦር በአስቸኳይ እንዲወጣና፣ይህም ማረጋገጥ በሚቻል መልኩ መሆን እንዳለበት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መናገራቸውን ኢምባሲው አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ የኤርትራ ሰራዊት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ መግባቱን በይፋ ባሳወቁበት መግለጫቸው፤ የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ከኤርትራ ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
የኤርትራና የአማራ ኃይሎች በትግራይ እየተባባሰ ባለው የሰብአዊ መብት ቀውስ ላይ አስዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል፤ ሁሉም አካላት ግጭቱን በአቸኳይ እንዲያቆሙ በውይይቱ ወቅት አንስተዋል ብሏል ኢምባሲው፡፡
የኤርትራ ወታደሮቿ በትግራይ መግባታቸውን ብታምንም፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ተሳትፈዋል የሚልው የአሜሪካና የተመድን ክስ አስተቀበልም፡፡ የአማራ ክልል መንግስትም አሁን የያዘው ቦታ የክልሉ አካል እንደሆነና በሰብአዊ መብት ጥሰት ተሳትፏል የሚለው ክስ እንደማይቀበል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ብሊንከን በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመመዝገብ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን በጋራመስራታቸውን በበጎነት ተቀብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጥቅምት 24፤2013 የፌደራል መንግስት፣ ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካሳወቀ በኋለ ሁለቱ አካላት ወደ ውጊያ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ጥቃቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል “የህግ ማስከበት ዘመቻ” ማካሄድ መጀመሩን ተከትሎ በተፈጠረ ውጊያ የሰብአዊ መብት ጥሰት አጋጥሟል፡፡