ኤርትራ ሰራዊቷ በትግራይ መኖሩን ለመጀመሪያ ጊዜ አምናለች፤ ለማስወጣት መስማማቷንም ለተመድ አስታውቃለች
የኤርትራ ወታደሮች አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ፈጽመዋል መባሉ "በህዝባችን ባህልና ታሪክ ላይ የተሰነዘረ የከፋ ጥቃት ነው" ነው ብለዋል አምባሳደሯ
አምባሳደር ሶፍያ ተስፋማርያም "አንዣቦ የነበረው ስጋት በመወገዱ የኤርትራ ሰራዊት ወጥቶ የኢትዮጵያ ሰራዊት በድንበር ላይ እንዲሰማራ ከስምምነት ላይ ተደርሰዋል" ብለዋል
በትግራይ ክልል፣ በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የኤርትራ ኃይሎች ድንበር ተሻግረው ወደ ትግራይ ክልል ገብተዋል የሚሉ ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ ሰራዊት ትግራይ ውስጥ መግባታቸውን አምኖ እንዲወጡ መስማማቱን ከመግለጹ ውጭ፣ የኤርትራ መንግስት ወታደሮቹ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው ስለመግባታቸው ያለው ነገር አልነበረም።
አሁን ግን የተባበሩት መንግሥታት(ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት ባካሄደው ውይይት ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ባለስልጣን የሆኑት ማርክ ሎውኮክ እና በምክር ቤቱ የአሜሪካ መልዕክተኛ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ላደረጉት ንግግር፤ ኤርትራ በተወካይዋ አማካኝነት ምለሽ ሰጥታለች፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ አምባሳደርና ቋሚ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ሶፊያ ተስፋማሪያም ለጸጥታው ጥባቃ ምክር ቤት ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡
አምባሳደሯ በፃፉት ደብዳቤ የኤርትራ ሠራዊትን በሚመለከት "አንዣቦ የነበረው ስጋት በአብዛኛው በመወገዱ ኤርትራና ኢትዮጵያ የኤርትራ ኃይሎችን ለማስወጣትና የኢትዮጵያ ሠራዊት በድንበር ላይ እንዲሰማራ ለማድረግ በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው አማካይነት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል" በማለት አረጋግጠዋል።
አምባሳደሯ አክለው በዝግ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የአሜሪካዋ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በሰነዘሩት "ተገቢ ያልሆነ" መግለጫ ላይ የኤርትራ መንግሥት ተቃውሞ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የመንግሥታቱ ድርጅት "በተደጋጋሚ ከተሰጠው ድርሻ ባሻገር በመሄድ ተቀባይነት የሌለው ገንቢ ያልሆነ ተግባራት ውስጥ ገብቷል" ሲሉ ከሰዋል አምባሳደሯ።
በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የአሜሪካ መልዕክተኛ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድም በዚሁ ጊዜ የአስገድዶ መድፈርና ጾታዊ ጥቃቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶችን ተከትሎ የኤርትራ ወታደሮች "በአስቸኳይ" ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ጠይቀው ነበር።
አምባሳደር ሶፊያ በደብዳቤያቸው ላይ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በግጭቱ ወቅት "ወሲባዊ ጥቃትና ረሃብ እንደ መሳሪያ ጥቅም ላይ ውሏል" በሚል የቀረበውን ክስ ሐሰተኛ ሲሉ በደብዳቤያቸው የተቃወሙት ሲሆን፤ የኤርትራ ወታደሮች አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ፈጽመዋል መባሉ "የሚያስቆጣ ብቻ ሳይሆን በህዝባችን ባህልና ታሪክ ላይ የተሰነዘረ የከፋ ጥቃት ነው" ብለውታል።
ህወሐት በፈጸመው ጥፋት በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ንጹሃን በምንም መልኩ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደማይገባ የገለፁት የኤርትራዋ አምባሳደር ፤ የሰብአዊ እርዳታን ማቅረብ የወቅቱ አንገብጋቢ ሥራ መሆን ይገባልም ነው ያሉት።
በትግራይ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ሐሙስ ዕለት ለአምስተኛ ጊዜ በተወያየው የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በግጭት ከተጎዳው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል "የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያመለክት ነገር የተባበሩት መንግሥታት ተቋማትም ሆኑ ሌሎች አብረውት የሚሰሩ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች እንዳላዩ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ባለስልጣን የሆኑት ማርክ ሎውኮክ መናገራቸውም የሚታወስ ነው።
ትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ድንበር ተሻግረው ገብተዋል የተባሉት የኤርትራ ወታደሮች የተለያዩ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን በተመለከተም ክስ ሲቀርብባቸው ቆይተዋል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ አምስት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን በዚህ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ላይ ለመምከርና መግለጫ ለመውጣት ምክር ቤቱ የሐሙስ ዕለቱን ጨምሮ ለአምስት ጊዜ ተሰብስቦ ተወያይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ማርክ ሎውኮክ ግጭቱ እንዲቆምና የበለጠ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር እንዲመቻች ጥያቄ አቅርበዋል።
ትግራይ ውስጥ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ጦር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር።
በትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አሃዙ በበርካታ ሺዎች ሊሆን እንደሚችል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይናገራሉ።
ከዚህ ባሻገርም በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች ግድያዎች፣ ጾታዊ ጥቃቶች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ዘረፋና የንብረት ውድመቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ አመልክተዋል።
በተጨማሪም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዳለው በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።