“የትግራይ አርሶ አደር ለማረስ የሚሆን በሬ እንኳን የለውም”-የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ
የግብርና ሚኒስቴር ለክልሉ የግብርና ዘርፍ 120 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ስለመባሉ እንደማያውቅ ገልጿል
የግብርናውን ሴክተር ወደ ነበረበት ለመመለስ “120 ቢልዮን ብር” እንደሚያስፈልግ የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል
በትግራይ የግብርናው ዘርፍ ስራዎች በአሁኑ ወቅት ካልተጀመሩ በሚቀጥሉት 5 እና 10 ዓመታት በዚህች ሀገር ታይቶ የማይታወቅ ‘ረሀብ’ ሊኖር እንደሚችል የትግራይ ጊዜያዊ መስተዳድር የግብርና ቢሮ ኃላፊ አባዲ ግርማይ (ዶ/ር) ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አባዲ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ በክልሉ የተካሔደው ጦርነት በግብርናው ዘርፍ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ፣ አርሶአደሩ የተጋረጠበትን ፈተና እና በክልሉ አሁን ያለውን የግብርና እንቅስቃሴ በተመለከተ ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ ያስከተለው ጉዳት
የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አባዲ ግርማይ (ዶ/ር) ፣ ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል በተከሰተው የበረሃ አምበጣ መንጋ ምክንያት 1/4ኛ የሚሆነው የክልሉ ምርት መውደሙን ገልጸዋል፡፡ ከአምበጣው በመቀጠል ደግሞ በክልሉ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የአርሶአደሩ ምርት መቃጠሉን እና መዘረፉን ነው ያስታወቁት፡፡
ዶ/ር አባዲ የደረሰው ውድመት እጅግ ከባድ መሆኑን አንስተው ካለፈው የመኸር ወቅት የተሰበሰበ “ምንም ምርት እንደሌለ”ም ገልጸዋል፡፡
70 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ምርት ከምዕራብና ደቡብ ትግራይ እንደሚሰበሰብ የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፣ “በምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ የነበረ ገበሬ አካባቢው በአማራ ኃይል ከተያዘ በኋላ ንብረቱንና ቀዬውን ትቶ ፣ ገሚሱ ወደ ሱዳን ገሚሱ ደግሞ ወደ ሌሎች የትግራይ አከባቢዎች ተፈናቅሏል” ብለዋል፡፡
በሌሎች የክልሉ ክፍሎች የተሰበሰበው ምርትም ቢሆን “በኤርትራ ሰራዊት ተዘርፏል ፤ እናም ምንም የቀረ ነገር የለም ፤ የትግራይ ገበሬ ባዶ እጁን ቀርቷል፤ የሚበላው እንኳን የለውም” ብለዋል ኃላፊው፡፡ የኤርትራ መንግስት በቅርቡ ለተባበሩት መንግስታት በጻፈው ደብዳቤ ፣ የሀገሪቱ ወታደሮች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ይፋ ቢያደርግም በወንጀል ድርጊት ግን አለመሳተፉን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
የግብርና ቢሮ ኃላፊው ዶ/ርአባዲ የትግራይ ገበሬን ሁኔታ ሲያስረዱ “የትግራይ ህዝብ ቤት ንብረቱ ተዘርፏል፤ ቋሚ ተክል እንኳን ሳይቀር ነው የወደመው” በማለት ገልፀዋል፡፡ የክልሉ አርሶአደር ያለበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ እንደሚያስጨንቃቸውም ነው ዶ/ር አባዲ የሚያስረዱት፡፡
አክለውም “ዘንድሮ ከመጪው ግንቦት ወር መጀመርያ አንስቶ የሆነ ነገር ማድረግ ካልተቻለ ፣ ለሚቀጥሉት 5/10 ዓመታት በዚህች ሀገር ታይቶ የማይታወቅ ረሀብና ቸነፈር ይኖራል” ሲሉም ያላቸውን የገዘፈ ስጋት አስቀምጠዋል፡፡
“አሁን ያለው አሳሳቢ ሁኔታ ድርቅ ከተጨመረበት ሁላችንም በህይወት የመኖራችን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ይህ ምንም ማመንታት የማያስፈልገው እውነታ ነው፡፡ ህይወት መቀጠል አለበት፤ ይህ ፖለቲካ አይደለም፡፡ ቢያንስ ለሚቀጥለው ዓመት ዘር መኖር አለበት፡፡ ገበሬው ተስፋ ማግኘት አለበት” ሲሉም ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡
“በገበሬው ላይ የደረሰው ችግር እጅግ ከባድ ነው፡፡ የሚያሳዝነው አርሶ አደሩ ለማረስ የሚሆን በሬ እንኳን የለውም” ብለዋል ዶ/ር አባዲ፡፡
የግብርና መዋቅሩ እና የግብዓት አቅርቦት ሁኔታ
በክልሉ ያለው ን የግብርና መዋቅር በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ፣ “ወረዳም ሆነ ቀበሌ የሚባል መዋቅር ስለፈራረሰና ስሌለለ እንደ ሴክተር ለመስራት ተቸግረናል” ሲሉ ዶ/ር አባዲ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ መስተዳድር ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወረዳ መዋቅር ስለመዘርጋቱ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ወረዳዎች በስራ ላይ እንደማይገኙ ነው ዶ/ር አባዲ የተናገሩት፡፡ በመሆኑም አስፈላጊውን እርዳታ በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚዎች ማዳረስ እንዳልተቻለ አብራርተዋል፡፡
ኃላፊው አጠቃለይ የግብርናውን ሴክትር ወደ ነበረበት ለመመለስም 120 ቢልዮን ብር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ከግብርናው ዘርፍ ጋር ተያይዞ ያለውን ጥልቅ ችግር ለጊዜያዊ መስተዳድሩ ፣ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለጠቅላይ ሚኒሰትር ቢሮ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል ያሉት ኃላፊው “ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢና ካበድ ነው” በማለትም የችግሩ መጠን አስረድተዋል፡፡
ለቀጣዩ የግብርና ስራ ባጠቃለይ 120 ሺህ ኩንታል ዘር እንደሚያስፈልግ ያነሱት ኃላፊው ፣ ዘር ለማቅረብ ከመንግስትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመስራት እየተሞከረ መሆኑንና ወደ መቀሌ ለማስገባት ጥረት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ “ማዳበርያም ማምጣት ጀምርናል፤ 300 ሺህ ኩንታል እጃችን ገብቷል” ሲሉም አክለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል 5,000 ኩንታል ዘር ለማቀውረብ ቃል ገብቶ 3,758 ኩንታል እጃቸው ላይ መግባቱንም የግብርና ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በግንቦት መጀመርያዎች የመሬት ዝግጅት ለመጀመር በተቻለ መጠን ከመንግስት ጋር በመተባበር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት የቢሮ ኃላፊው ጉዳዩ ከመንግስት ባሻገር የግል ድርጅቶችን እና የግለሰቦችን ከፍተኛ ድጋፍም እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት ምን ይላል?
አል ዐይን አማርኛ የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ በክልሉ ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ያነሷቸውን ጉዳዮች መነሻ በማድረግ ግብርና ሚኒስቴርን አናግሯል፡፡
በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ የእርሻ ልማት ዘርፍ ተወካይ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ግርማሜ ጋሩማ “በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል የነበረው ሁሉም ምርት ወድሟል” ስለመባሉም ይሁን “ግብርናውን ወደ ነበረበት ለመመለስ 120 ቢሊዮን ብር የገንዘብ መጠን ያስፈልጋል” ስለተባለው ነገር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴዔታው አክለውም ለትግራይ ክልል ለመጪው የመኸር ወቅት ለእርሻ ስራ የሚውሉ የምርጥ ዘር ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
“የክልሉ ግብርና ቢሮ የጠቀሰው ችግር በተባለው ልክ ካለም ፣ በአጠቃላይ ትግራይን መልሶ ለመገንባት በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ስላለ በዚያ በኩል ለችግሩ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል”ም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው።