“በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ጥሰቶች አሁንም መሻሻሎች እየታዩ አይደለም”- የአውሮፓ ህብረት
ሀቪስቶ የትግራይ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ “ረሀብ” ሊከሰት እንደሚችልም ስጋታቸው ገልፀዋል
የህብረቱ ልዩ መልእክተኛ ፔካ ሀቪስቶ በክልሉ ያለውን ግጭት ለመፍታት “ብቸኛው መፍትሄ ድርድር” ነው ብለዋል
በትግራይ ክልል ያለው የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱን ከቀናት በፊት ትግራይን የጎበኙት የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልእክተኛ የፊንላንዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሀቪስቶ ተናገሩ፡፡
ልዩ መልእክተኛው ከሲ.ኤን.ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ “በትግራይ ባለው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ መሻሻሎች እየታዩ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሀቪስቶ በክልሉ በነበራቸው ቆይታ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘውን ‘የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል’ን የመጎብኘት እድል እንደነበራቸው ያነሱ ሲሆን ሆስፒታሉ ጉዳት በደረሰባቸው ንጹሃን ዜጎች ተጨናንቆ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌሎች የህክምና መሰረተ ልማቶች መዘረፋቸውንና መውደማቸውንም ነው ሃቪስቶ የገለጹት፡፡
“እጅግ አሳሳቢው ነገር ሰብዓዊ ጥቃቶቹ አሁንም አለመቆማቸው ነው” ብለዋል ልዩ መልዕክተኛው፡፡
“በዋናነት ምናልባትም ከአንድ ሺ ሊበልጡ የሚችሉ አዲስ የምዕራብ ትግራይ አካባቢ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ገልጸውልኛል”ም ነው ያሉት ሃቪስቶ፡፡
ይህ አሁንም ዜጎች ተገደው የሚፈናቀሉበት ሁኔታ እንዳለ የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ልዩ መልዕክተኛው በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት በተለይም በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ፖለቲካና ግጭት የካበተ ልምድ አላቸው እንደ ሲኤንኤን ገለጻ፡፡
ይህን ተከትሎ በትግራይ ያጋጠመው ችግር “በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ የሚችልበት አግባብ አለወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ከድርድር የተሻለ መፍትሔ” እንደሌለ በመጠቆም የግጭቱ ተዋናዮች “ሊደራደሩ ይገባል” ብለዋል፡፡
ሀቪስቶ “እንደ አውሮፓ ህብረት ከሆነ ብቸኛው መፍትሄ ሁሉም የጦርነቱ ተዋናዮች ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ ሰራዊት፣ የአማራ ሚሊሻ እንዲሁም በኪስ አካባቢዎች የሚዋጉ የህወሓት ኃይሎች ሊደራደሩ ይገባል” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
“ተፈፀሙ” የተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች “በወጉ ሊመረመሩ” እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
“ግጭቱ አሁንም ቀጥሏል” ያሉም ሲሆን ንጹሃን ዜጎች አሁንም በግጭቱ መካከል እንደሚገኙ፣ ዝርፊያ መቀጠሉን እና አርሶ አደሮች የእርሻ ስራዎቻቸውን በአግባቡ ለማከናወን አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህ “ዜጎችን ለከፋ አዲስ ርሃብ እንያዳያጋልጥ” መስጋታቸውንም ነው ሃቪስቶ የተናገሩት፡፡
ልዩ መልዕክተኛ ይህን ይበሉ እንጂ ኢትዮጵያ በክልሉ ያለው የሰብዓዊ መብቶች የአያያዝ ሁኔታ መሻሻሉን ስትገልጽ ነበር፡፡
በክልሉ በመደረግ ላይ ካሉት ሰብዓዊ እርዳታዎች 70 በመቶ ያህሉ በመንግስት መሸፈናቸውን በመጠቆምም ለ4.5 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ መቻሉንም አስታውቃለች፡፡
“የኤርትራ ወታደሮች እንደሚወጡ የማድረጉ ሂደት እንዲፋጠን እየተሰራ ነው” መባሉም የሚታወስ ነው፡፡
በክልሉ በመካሄድ ላይ ካለው ዘመቻ ጋር በተያያዘ ዛሬ መግለጫ የሰጡት የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ዘርፍ ዋና አስተባባሪ ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ የህወሓት ቡድን “በትግራይ 8 አካባቢዎች ሲያደርግ የነበረው የሽፍታ እንቅሰቃሴ” በመከላከያ ሠራዊቱ መደምሰሱን አስታውቀዋል፡፡