48 የዓለማችን ቢሊየነሮች በኪሳራ ምክንያት ወደ ሚሊየነርነት ዝቅ ማለታቸው ተገለጸ
በ2022 ዓመት የዓለማችን ባለሀብቶች ሁለት ትሪሊዮን ዶላር መክሰራቸው ተገልጿል
እንደ ሀገር አሜሪካዊያን ባለሀብቶች ብዙ ኪሳራ አስመዝግበዋል ተብሏል
በ2022 ዓመት የዓለማችን ባለሀብቶች ሁለት ትሪሊዮን ዶላር መክሰራቸው ተገለጸ።
በቅርቡ የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ለዓለማችን ባለጸጋዎች መልካም እንዳልነበር ትኩረቱን በምጣኔ ሀብት ዘገባዎች ላይ የሚያደርገው ፎርብስ በድረገጹ አስነብቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የዓለማችን ባለሃብቶች ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ያስመዘገቡ ሲሆን አሜሪካዊ ባለሀብቶች ደግሞ በአንጻራዊነት ብዙ ኪሳራ ማስመዝገባቸው ተገልጿል።
በፈረንጆቹ 2020 እና 2021 ዓመት ለባለሀብቶች ብዙ ትርፍ እንዲያስመዘግቡ ያገዘ ቢሆንም የተጠናቀቀው 2022 ዓመት ግን ኪሳራን አስከትሏል ተብሏል።
በአውሮፓ የተከሰተው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት፣ የአክስዮን ገበያ መቀዛቀዝ እና የዋጋ ግሽበት ለዓለማችን ባለጸጋዎች ገቢ መቀነስ ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የዓለማችን ባለጸጋዎች በአጠቃላይ 13 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዶላር ሀብት የነበራቸው ሲሆን በ2022 ኪሳራ ማስመዝገባቸውን ተከትሎ የጠቅላላ ሀብታቸው ወደ 11 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱ ተገልጿል።
ኪሳራውን ተከትሎም የቢሊየነሮች ቁጥርም ከ2 ሺህ 671 ወደ 2 ሺህ 523 ዝቅ ሊል መቻሉን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ታዋቂው ሙዚቀኛ ካንየ ዌስትን ጨምሮ ሳም ባንክማን እና የሪቪያን መስራቹ አርጂ ስካሪንጅ ከቢሊየነርነት ደረጃቸው ወደ ሚሊየነርነት ዝቅ ያሉ ባለሀብቶች ናቸው።
የተጠናቀቀው 2022 ዓመት በሁሉም ቢሊየነሮች ላይ ኪሳራ ያስመዘገቡበት ዓመት ቢሆንም 300 የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ግን ከሁሉም ከፍተኛ ኪሳራ ማስመዝገባቸው ተገልጿል።
በተለይም በጄፍ ቤዞፍ የተመሰረተው አማዞን ኩባንያ 80 ቢሊዮን ኪሳራ ሲያስመዘግብ፣ ጎግል ኩባንያ 40 ቢሊዮን ዶላር፣ ቢል ጌት 20 ቢሊዮን ዶላር፣ የሜታ ኩባንያ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ 78 ቢሊዮን ዶላር፣ የትዊትር እና ቴስላ ኩባንያ ባለቤቱ ኢለን መስክ 200 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ማስመዝገባቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ በ2022 ዓመት አሜሪካዊያን ባለሃብቶች 660 ቢሊዮን ዶላር በመክሰር ቀዳሚ ሲሆኑ የቻይና ባለጸጋዎች ደግሞ 620 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ በማስመዝገብ በሁለተኝነት ሲቀመጡ የአሊባባ ኩባንያ ባለቤቱ ጃክ ማ 13 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡
ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ሩሲያ ደግሞ በባለሃብቶቿ ላይ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት 150 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ማስመዝገቧ ተገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን የእስያ ባለሃብቶች በአንጻራዊነት የተጠናቀቀው 2022 ዓመት ምርጥ ዓመት እንደነበረላቸው ተገልጿል፡፡
በተለይም በስፖርት ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት አሜሪካዊው ቶድ ቦህሊ እና ዲዛይነሩ ቶም ፎርድ 11 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ሲያገኙ ቻይናዊው ኮሊን ዜንግ እና ኢንዶኔዢያዊው የከሰል ድንጋይ ነጋዴ ሎው ተክ ክዋንግ በድምሩ 16 ቢሊዮን ዶላር ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡
ከቀናት በፊት የተጠናቀቀው 2022 ዓመት ለሕንዳዊው ጉዋተም አዳኒ በታሪኩ ከፍተኛውን ትርፍ ያገኘበት ዓመት ሲሆን በሎጅስቲክስ እና ሀይል ልማት የተሰማሩት ኩባንያዎቹ በድምሩ 55 ቢሊዮን ትርፍ አስገኝተውለታል ተብሏል፡፡
ይህ ሕንዳዊ ባለጸጋ ከፍተኛ ትርፍ ማትረፉን ተከትሎ አጠቃላይ የሐብት መጠኑ ወደ 134 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሲል ሶስተኛው የዓለማችን ባለጸጋ ለመሆንም በቅቷል፡፡