ባለፀጋው ኤሎን መስክ የ200 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጠማቸው
የኤሎን መስክ 44 ቢሊዮን ዶላር የትዊተር ግዢ ለሀብታቸው ማደግ የፈየደው የለም ነው የተባለው
የቴስላ አክሲዮን ማሽቆልቆሉን ተከትሎ የመስክ ሃብት ወደ 137 ቢሊዮን ዶላር ወርዷል
የቴስላ ዋና ስራ አስፈጻሚና የትዊትር በለቤቱ ኤሎን መስክ ከሀብታቸው 200 ቢሊዮን ዶላር በማጣት የመጀመሪያው ሰው ሆነዋል ሲል የብሉምበርግ ዘገባ አመልክቷል።
የ51 አመቱ መስክ ከዚህ ቀደም በጥር 2021 ከአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስ በመቀጠል የቢሊዮን ዶላሮች ሀብት በማካበት ሁለተኛው ሰው ሆነው እንደነበር አይዘነጋም።
ከዛም አልፎ መስክ የሀብት መጠናቸውን 340 ቢሊዮን ዶላር በመምታቱ እስከ ባለፈው ወር ድረስ የዓለማችን ባለጸጋ ሰው ማዕረግን ደረጃ ይዘው ነበር።
ይሁን እንጅ በቅርቡ የቴስላ አክሲዮን ማሽቆልቆሉን ተከትሎ የመስክ ሃብት ወደ 137 ቢሊዮን ዶላር ወርዷል።
በዚህም መስክ በፈረንሳይ ግዙፉ የቅንጦት ኤልቪኤምኤች ዋና ስራ አስፈጻሚ በርናርድ አርኖት ተበልጠው ከዙፋናቸው ለቀዋል፡፡
የብሉምበርግ መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ በ2022 ቴስላ በአክሲዮን ገበያው ውስጥ ሁለት ሶስተኛውን ዋጋ አጥቷል፡፡
ኩባንያው የመኪናውን ክምችት ለማጽዳት ባደረገው ጥረት አነስተኛ ሽያጭ ማድረጉን ካወጀ በኋላ በቴስላ የመኪና ገዢ ፍላጎት እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳዩ መረጃዎች ባለፈው ወር ሲወጡም ተስተውለዋል፡፡
ኩባንያው ከአመቱ መጨረሻ በፊት መኪና ለሚቀበሉ ገዢዎች ሁለት ቅናሾችን ( መጀመሪያ ላይ የ 3 ሺህ 750 ዶላር ቅናሽ አድርጓል፣ ከዚያም ቅናሹን በእጥፍ ወደ 7ሺህ 500 ዶላር አሳድጓል) ማቅረቡ በደንበኞቹ ዘንዳ እምነት እንዲያጣ ምክንያት ነበሩም ነው የተባለው፡፡
ባለሀብቶች በኩባንያው ላይ ያላቸው እምነት በ37 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉም ነው ዘገባው የሚያመከለክተው፡፡
ተቺዎች “ለመሆኑ ቴስላ እንደፈረንጆቹ በ2022 መጀመሪያ ላይ የነበረው 1 ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ አለውን..? የሚል ጥያቄ አስከማንሳትም ደርሰዋል፡፡
የኤሎን መስክ 44 ቢሊዮን ዶላር የትዊተር ግዢ የቴስላን አክሲዮኖችም ሆነ የግል ሀብታቸው ከማሳደግ አንጻር የፈየደው የለም ነው የተባለው፡፡
የቴስላ ትልቁ ባለድርሻ የሆኑት ኤሎን መስክ በሚያዝያ ወር በትዊተር ላይ ፍላጎት እንዳላቸው ካሳወቁበት ጊዜ ጀምሮ 23 ቢሊዮን ዶላር አክሲዮኖችን ሸጠዋል።
የኤሎን መስክ የማያቋርጥ ትዊቶች እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ባህሪይ፤ በተለይም እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚነት ከተረከቡ በኋላ፤ ለትልቅ እና የበለጠ ዋጋ ላለው ኩባንያ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ የሚፈልጓቸው የቴስላ ባለሀብቶችን አስቆጥቷል፡፡
ኤሎን መስክ ግን የቴስላ ባለሃብቶች ትችት እንደማይቀበሉት ይገልጻሉ፡፡
"ትዊተርን ከተረከብኩ በኋላ ያመለጠ የቴስላ ስብሰባ ካለ እስኪ ንገሩኝ?" ሲሉም ራሳቸው ተከላክለዋል ኤሎን መስክ፡፡
የመስክን ሃሳብ የሚጋሩት ሌሎችም ቴስላ ጊዜያዊ መንገራገጭ ቢገጥመውም ወደ ነበረበት የስኬት ማማ ተመልሶ ሊመጣ ይችላል ኤሎን ማስክም እንዲሁ እንደገና በዓለም ላይ እጅግ ባለጸጋ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምታቸው አስቀምጠዋል፡፡