ሩሲያን ለቀው የወጡ የምዕራባውያን ኩባንያዎች 240 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰባቸው ተገለጸ
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በርካታ የአውሮፓ ኩባንያዎች ሞስኮን ለቀው ወጥተዋል
የአሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ጀርመን ኩባንያዎች ማዕቀቦችን በመፍራት ሞስኮን ለቀዋል
ሞስኮን ለቀው የወጡ የምዕራባውያን ኩባንያዎች 240 ቢሊዮን ኪሳራ እንደደረሰባቸው ተገለጸ።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሰባት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም በሚል በአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
ማዕቀቡን ተከትሎም በሩሲያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩ ኩባንያዎች ሞስኮን ለቀው ወጥተዋል።
እነዚህ የአሜሪካ እና ምዕራባውያን ኩባንያዎች ከሩሲያ በመልቀቃቸው እና ምርታቸውን በማቋረጣቸው ምክንያት 240 ቢሊዮን ዶላር መክሰራቸውን አርቲ ዘግቧል።
ሩስያን ለቀው ከወጡ የምዕራባውያን ኩባንያዎች መካከል የአሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ጀርመን ተቋማት ዋነኞቹ ሲሆኑ የሶስቱ ሀገራት ድርጅቶች እስከ 90 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማጣታቸውም ተገልጿል።
ይህ ጦርነት በዓለም የምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ከማስከተሉ ባለፈ በሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይም እክሎችን በማስከተል ላይ ነው።
ሩሲያ ለልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን ግዛት የላከችው ጦር በርካታ ግዛቶችን ተቆጣጥሮ ከዚህ ውስጥ አራቱ ማለትም ኬርሰን፣ ዛፖራዬዝ፣ ዶንተስክ፣ ዶምብአስ እና ሉሀንስ በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ተጠቃለዋል።
የሩሲያን ውሳኔ ተከትሎም አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሞስኮ ላይ አዲስ ማዕቀቦችን የጣሉ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ ደግሞ አዲስ ጭማሪ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።